የጋምቤላ ክልል ዳያስፖራዎችን ለመቀበልዝግጅት እያደረገ ነው

80

ጋምቤላ ታህሳስ 21/2014 (ኢዜአ) ከውጭ የሚመጡ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ለመቀበል የጋምቤላ ክልል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የክልሉ ዳያስፖራ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ኦኬሎ ኮም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ    ያቀረቡትን  ጥሪ ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ያሉትን ዳያስፖራዎች በልዩ አቀባበል ለማስተናገድ ትኩረት ተሰጥቷል።

የክልሉ ተወላጆችን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ክልሉ ለማስተናገድ ሰፊ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ኮሚቴዎች ተቋቁመው ሆቴሎችንና የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ምቹ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በክልሉ ለተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ሊውሉ የሚችሉ ሰፊ የመሬት፣ የውሃ፣ የማዕድንና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን በማስተዋወቅ በልማቱ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ዳያስፖራዎች እንደሚስተናገዱ  አስታውቀዋል።

በተለይም በማጃንግ ፣አኝዋሃና ኑዌር ዞኖች የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሐይቆች፣ወንዞች ፣የተፈጥሮ ደን ሀብትና ሌሎች መስቦችን ለዳያስፖራዎች ለማስጎብኝት መታቀዱንም ገልጸዋል።

በክልሉ የተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳድር ስራዎች በማስጎብኘት የክልሉ ልማት ያለበትን ደረጃ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ዝግጅት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።      

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም