አትሌት ለተሰንበት ግደይ የዓመቱ 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ አፍሪካውያን ውስጥ ተካተተች

782

ታህሳስ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኒው አፍሪካ መፅሔት በፈረንጆቹ 2021 ተፅዕኖ ፈጣሪ ነበሩ ያላቸውን 100 አፍሪካውያን ዝርዝር ይፋ አድርጓል።

በዚህም በዓመቱ ዓለም በተፅዕኖ ስር ሆና ብታሳልፍም ብዙ አንፀባራቂ ታሪኮች የተከናወኑበት ነበር ብሏል።

በተለይ ተፅዕኖ ፈጣሪ አፍሪካውያን ብዙ ድሎችም መቀዳጀታቸውን ያስታወሰው መፅሄቱ በዚህም በተለያዩ ዘርፎች 100 ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን መምረጡን ገልጿል።

በስፖርቱ ዘርፍ ከተመረጡ ተፅጽኖ ፈጣሪዎች መካከል ኢትዮጵያዊቷ ለተሰንበት ግደይ ቀዳሚዋ ሆናለች።

መፅሔቱ የለተሰንበትን የተፅዕኖ ፈጣሪነት ታሪክ ሲጀምር ክብረ ወሰኖችን በቀላሉ የሰባበረች ብሎላታል።

ኢትዮጵያ ከአበበ ቢቂላ እስከ ቀነኒሳ በቀለ፣ ከብርሃኔ አደሬ እስከ ጥሩነሽ ዲባባ ጀግኗ ሯጮችን ያፈራች ሀገር ናት ይላል መፅሄቱ።

እነ ቀነኒሳ እና ጥሩነሽ ከሩጫው ዓለም ቀስ በቀስ እየወጡ ቢሆንም የ23 ዓመቷ ለተሰንበት ግደይ በእነሱ የድል ቦታ ተተክታለች ነው ያለው።

ለተሰንበት በአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ተይዞ የነበረውን የ5 ሺህ ሜትር ክብርወሰን በ2020 ጥቅምት ወር በእጇ ስታስገባ ዓለም መደነቁን ፅፏል።

ባሳለፍነው ሃምሌ ወር ደግሞ የ10 ሺህ ሜትር የዓለም ክብረወሰንን በእጇ አስገብታለች።

ጥቅምት ወር ላይ ቫሌንሺያ ውስጥ በተካሄደ የግማሽ ማራቶን ውድድር ለተሰንበት 1 ሰዓት ከ02 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ በመግባት የዓለምን የግማሽ ማራቶን ክብረወሰን በእጇ አስገብታ ዓለምን አስገርማለች።

በዚህም የስፖርት ውድድር ዘጋቢዎች ለተሰንበት ወንዶችን መፎካከር የሚያስችል ድንቅ ብቃት አላት አስብሏቸዋል።

ኒው አፍሪካ መፅሔት በመጪዎቹ ዓመታት ሌሎች ክብረወሰኖችን በመሰባበር የዓለም የአትሌቲክስ ኮከብ የኢትዮጵያ የስፖርት አምባሳደር የመሆን እድሉ እጇ ላይ መሆኑን አትቷል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም