"ዛሬም ነገም ለወገን ፈጥኖ ደራሾች እኛው እንሁን" - ብፁዕ አቡነ አብርሃም

298


ባህር ዳር፣ ታህሳስ 21/2014(ኢዜአ) "ለተቸገሩ ወገኖች ደራሽ ከኛ በላይ ሌላ ሊኖር ስለማይገባ ዛሬም ነገም ለወገን ደራሾች እንሁን" ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ተናገሩ።

የባህር ዳር ሀገረ ስብከት በስሯ ከሚገኙ አብያተክርስቲያናት ሠራተኞችና ከራሷ በማውጣት በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች ዛሬ የ4 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጋለች።


ብፁዕ አቡነ አብርሃም ድጋፉን ሲያስረክቡ እንዳሉት፣ የተፈናቀሉትን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ቤተክርስቲያን የበኩሏን አስተዋጽኦ እያደረገች ነው።


"ለወገን ደራሽ ከኛ በላይ ማንም ሊኖር አይችልም" ያሉት ብፁዕ አቡነ አብርሃም፤ "የቤተክርስቲያን ተግባርና መልዕክት ዛሬም ነገም ለወገን ደራሽ እንሁን ነው" ብለዋል።


ቤተክርስቲያን ከዚህ ቀደምም የተለያዩ ድጋፎችን ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰው፣ ዛሬም የከተማ አስተዳደሩን ጥሪ በመቀበል ከመንግስት ጎን መሆኗን ለማረጋገጥ የ4 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጓን ተናግረዋል።


ድጋፉ የተደረገው በሀገረ ስብከቱ ስር ካሉ 40 አብያተክርስቲያናት ሠራተኞችና ቤተክርስቲያኗ ከምዕመናኑ ከምታሰባስበው ገንዘብ ላይ በመቀነስ መሆኑን አመላክተዋል።


ቤተክርስቲያኗም በጦርነቱ ክፉኛ እንደተጎዳች ያወሱት ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ "ቤተክርስቲያኗ የተቸገረ ወገን እያለ የፈረሱ አብያተክርስቲያናትን ቀድሜ ልስራ አላለችም" ብለዋል።


ይልቁንም ያለምንም የሃይማኖት ልዩነት ቅድሚያ የተገዱትን ወገኖች መልሶ ለማቋቋምና የፈረሱ ቤቶችንና ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።


በቀጣይም በሀገረ ስብከቱ ስር የሚገኙ አድባራትንና ገዳማትን በማስተባበር ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።


የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው፤ ቤተ ክርስቲያኗ የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኗን ተናግረዋል።


የባህር ዳር ሀገረ ስብከት የከተማ አስተዳደሩን ጥሪ በመቀበል፤ በተለይ ድጋፉ እንዲደረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ የሀገረ ስብከቱ አመራሮች ጭምር ምስጋና አቅርበዋል።


በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ጥቃት የተጎዱና የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ዶክተር ድረስ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም