የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት ከሰላምና ደኅንነት ወደ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እያደገ ነው

85
አዲስ አበባ ነሃሴ 21/2010 የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነትን ከሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ወደ ምጣኔ ሃብታዊ ትስስር ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ገለጹ። የሶማሊያ መንግሥት እስኪጠናከር ድረስ ኢትዮጵያ በፖለቲካው መስክ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አምባሳደር ጀማል ሙስጠፋ ተናግረዋል። አምባሳደሩ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ከገባችበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን አገሪቱን እየደገፈች ትገኛለች። ከአፍሪካ ኅብረትና ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ጋር በመተባበርም አገሪቱን መልሶ ለማቋቋም የተለያየ ተግባር አከናውናለች። በተለይም በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ሠላም አስከባሪ ሠራዊት (አሚሶም) ሥር ከአገሪቱ ህዝብ ጋር በመቀናጀት ሽብርተኝነት በመዋጋት ስኬታማ ግዳጅ ፈጽማለች። በፖለቲካውና በሌላው ዘርፍ ያለው የአገራቱ ግንኙነት መጠናከሩን ገልጸው አጋርነቱን ይበልጥ ለማጠናከርም አሁንም በመሪዎች ደረጃ ስምምነት ተደርሷል ብለዋል። በተለይም የአገራቱ ግንኙነት ከሰላምና ደኅንነት ጥበቃ ሥራ ወደ ምጣኔ ሃብታዊ ትስስር ለማሸጋገር ሥራዎች በዕቅድ መያዛቸውን ነው አምባሳደሩ የገለጹት። ኢትዮጵያ የሶማሊያ መንግሥት እስኪጠናከር ድረስ በተለይም በሠላምና ደህንነት ዘርፍ ላይ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል። ለአሚሶም ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩና ጠንካራ ሶማሊያን ለመፍጠር ርብርብ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። በሌላ በኩል ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከ20 ሺህ በላይ የሶማሊያ ዜግነት ያላቸው ተማሪዎችና ሠራተኞች የትምህርትና ሥልጠና ድጋፍ ማግኘታቸውንም ጠቅሰዋል። ይህም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ በማድረስ እነዚህ ዜጎች የአምባሳደርነት ሚናቸው ከፍተኛ እንደሚሆን ነው አምባሳደሩ የተናገሩት። ኢትዮጵያ በሶማሊያ የዛሬ 11 ዓመት ገደማ ነው ኤምባሲዋን የከፈተችው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም