ወደ ውጭ ከተላከ ቡና 520 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኘ

138


ዲላ፤ ታህሳስ 20/2014(ኢዜአ) ባለፉት አምስት ወራት ወደ ውጭ ከተላከ የቡና ምርት ሽያጭ 520 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያና ይርጋጨፌ ወረዳዎች የቡና ልማትና ምርት ዝግጅት እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።
በዚህ ወቅት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ እንደገለጹት፤ በተያዘው ዓመት ጥራቱን የጠበቀ 280 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት እየተሰራ ነው።
ከዚህም ባለፉት 5 ወራት ከ140 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከ520 ሚለዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር ማግኘት መቻሉን አስታውቀዋል።


ይህም በመጠንም ሆነ በገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር ከእጥፍ በላይ ብልጫ እንዳለውና ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ ታሪክ ከፍተኛው መሆኑን ተናግረዋል።
ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው ቡና 70 በመቶው ጥራቱን የጠበቀና ተወዳዳሪ እንዲሆን ጥራት ያለውን ቡና ላቀረበ አርሶ አደር የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ መደረጉንም ዶክተር አዱኛ አመላክተዋል።
በአርሶ አደሩ ማሳ በጉንደላና በአዲስ ተከላ እየተከናወነ ያለው የቡና እድሳት በዓለም ገበያ የሚቀርበው ቡና የጥረት ደረጃው እንዲሻሻል እገዛ ከማድረጉ ባለፈ እቅዱን ለማሳካትም ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን አስረድተዋል።
ለአርሶ አደሩ የገበያ አማራጮችን ከማስፋት ጀምሮ እቅዱን ለማሳካት የሚያስችል የፖሊሲ ለውጥ ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ ጥራቱን የጠበቀ ቡና በፍጥነት ተሰብስቦ ለማዕከለዊ ገበያ ከማቅረብ ባለፈ የእሴት ሰንሰለቱንና የምርት ብክነትን ለመቀነስ በተደረገው ጥረት ውጤት መገኘቱን ነው ያነሱት።
በክልሉ የቡና ምርት ጥራትን በማሻሻል ገቢን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ናቸው።
በተለይ አርሶ አደሩ ልዩ ጣዕም ያለው ቡና አዘጋጅቶ በቀጥታ ለውጭ ገበያ እንዲያቀርብ በማድረግ የቡና ጥራትና የአርሶ አደሩን ገቢ ማሳደግ መቻሉን አስረድተዋል።
ክልሉ ቡና ላይ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ በጌዴኦ ዞን የተጀመረውን የቡና እድሳት ተከትሎ የተገኘውን ምርታማነትና ጥራት ወደ ሌሎች ቡና አምራች አካባቢዎች ለማስፋት በትኩረት መሰራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ በበኩላቸው፤ በዞኑ በተያዘው ዓመት ከ14 ሚሊዮን በላይ ያረጁ የቡና ዛፎችን በአዲስ ለመተካት በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
ያለንን አቅም ተጠቅመን ሀገራችንን ከጠባቂነት የምናላቅቅበት ወቅት አሁን ነው ያሉት አስተዳዳሪው፤ በተለይ በኩታ ገጠም የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ለሚያለሙ አርሶ አደሮች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በመስክ ምልከታው ላይ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳን ጨምሮ የፌዴራልና የደቡብ ክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ በክልሉ የቡና አብቃይ ዞንና ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ሌሎች የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም