የመዲናዋ ነዋሪዎች ኢትዮጵያን ብለው ለመጡ እንግዶች በጨዋነት መንፈስ ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል

151


ታህሳስ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመዲናዋ ነዋሪዎች ኢትዮጵያን ብለው ለመጡ እንግዶች በጨዋነት መንፈስ ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የስራ፣ የኢንተርፕራይዝና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡትን ኢትዮጵያዊያንና የኢትጵያን ወዳጆች ታሳቢ ያደረገ ኤግዚቢሽንና ባዛር ዛሬ በእንጦጦ ፓርክ ተከፍቷል።

ኤግዚቢሽንና ባዛሩን የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የስራ፣ የኢንተርፕራይዝና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ፤ የከተማዋ ነዋሪዎች እንግዶቹን በኢትዮጵያዊ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንዲያስተናግዱ ጠይቀዋል።

እንግዶቹ በቆይታቸው የተሻለ ነገር እንደሚመለከቱና ስለ ኢትዮጵያ በጎ ነገር እንዲያሰቡ መንግስት የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል ብለዋል።

በዚህም በመዲናዋ በዓላትን ታሳቢ ያደረጉ ስምንት ባዛርና ኤግዚቢሽኖች ተዘጋጅተዋል ነው ያሉት።

የተለያዩ ጉብኝቶች፣ ስፖርታዊ ውድድሮችና ኮንሰርቶችን ጨምሮ የተለያዩ መዝናኛዎች መዘጋጀታቸውንም እንዲሁ አንስተዋል።

በመሆኑም የመዲናዋ ነዋሪዎች ኢትዮጵያን ብለው የመጡ እንግዶች ቆይታቸው በደስታ የተሞላ እንዲሆን አስፍላጊውን ትብብር የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት፡፡

በባዛርና ኤግዚቢሽን መክፈቻው ላይ ያገኘናቸው አቶ ዮሴፍ ሰለሞን ኑሯቸውን በሆላንድ አገር ካደረጉ 15 ዓመታት መቆጠራቸውን ነግረውናል፡፡

”ማንም ሰው የሌላ አገር ዜግነት ቢኖረው አገሩን አይረሳም” የሚሉት አቶ ዮሴፍ፤ ኢትዮጵያ ሁሌም በልባቸው ውስጥ እንዳለች ይናገራሉ፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ በውጪ አገር ሆነው ስለ ኢትዮጵያ የሚሰሙት ያገኙት ነገር ፈጽሞ የተለያየ መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያውያን አንድነት ይበልጥ መጠናከሩን ተናግረዋል፡፡

የኤግዚቢሽንና ባዛሩ አዘጋጅ አቶ የተማረ አወቀ በበኩላቸው በእንጦጦ ፓርክ የተዘጋጀው ባዛር በአገር ውስጥ ምርት ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህም ዳያስፖራው ከአገሩ ርቆ እንደመቆየቱ የአገር ባህል ምርቶችን እንዲሸምትና ጥሩ ማስታወሻ እንዲያስቀምጥ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት እየመጡ ነው።

እስካሁን ለመጡ እንግዶችም ዛሬ በወዳጅነት አደባባይ መንግስታዊ አቀባበል መደረጉ ይታወቃል።