በፍቼ አንዲት እናት አራት ሕፃናትን በአንድ ጊዜ ተገላገሉ

204


ፍቼ ታህሳስ 20/2014/ኢዜአ/ በፍቼ ከተማ አንዲት እናት ባልተለመደ ሁኔታ አራት ሕፃናትን በአንድ ጊዜ መገላገላቸውን የፍቼ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስታወቀ፡፡
የሆስፒታሉ የእናቶችና ሕፃናት ጤና የቀዶ ሕክምና ባለሙያ አቶ ግርማ ፈይሣ ለኢዜአ እንደገለፁት ከደገም ወረዳ የተላኩት እናት ሕጻናቱን በቀዶ ሕክምና የተገላገሉት ትናንት ከምሽቱ 5፡3ዐ ላይ ነው።
ወይዘሮ ረቢ እሸቴ ደበሌ የተባሉት ሴት በአንድ ጊዜ የተገላገሉት ሶስት ሴቶችና አንድ ወንድ ሕጻናት መሆኑን ተናግረዋል።
ሕፃናቱ ከ1 ነጥብ 4 እስከ 1 ነጥብ 8 ኪሎ ግራም የሚመዝን ክብደት እንዳላቸውም ነው የጠቀሱት።
ህጻናቱ በሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች እንክብካቤ እየተደረገላቸው በመልካም የጤንነት ሁኔታ እንደሚገኙ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡
ወይዘሮ ረቢ የ28 ዓመት ወጣት ሲሆኑ ከዚህ በፊት ሁለት ልጆችን በተለያየ ጊዜ መውለዳቸውን አስታውሰዋል።
ወላዷ በአሁኑ የወሊድ ጊዜያቸው በሆስፒታሉ በእናቶችና ሕፃናት ክብካቤ ክፍል ውስጥ ለሁለት ሳምንታት ተኝተው የህክምና ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸውን አቶ ግርማ አስታውቀዋል፡፡