አገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው ጉዳይ መክረው መፍትሔ እንዲያስቀምጡ ያግዛል

209

ታህሳስ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው ጉዳይ መክረው መፍትሔ እንዲያስቀምጡ የሚያስችል ነው፡፡


የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 2ኛ ልዩ ስብሰባው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ለማቋቋም የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።

የረቂቅ አዋጁን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ የሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለምክር ቤቱ አቅርቧል።

የኮሚሽኑ መቋቋም በፖለቲካና በሐሳብ መሪዎች መካከል መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ ሰፊ ልዩነቶችን በመፍታት አገራዊ አንድነት ለማምጣት እንደሚያስችል በውሳኔ ሐሳቡ ተካቷል።

መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚታየውን ልዩነትና አለመግባባት ለመፍታት ሰፋፊ አገራዊ የህዝብ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ ለማካሄድ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ባደረጉት ውይይት እንዲሻሻሉና እንዲጨመሩ ያነሷቸው ሐሳቦች ማስተካከያ ተደርጎባቸው በውሳኔ ሀሳቡ መካተታቸው ተጠቁሟል።

የምክር ቤት አባላትም የአዋጁ አስፈላጊነትና ወቅታዊነት ላይ በመስማማት በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን አንስተዋል።

መግቢያ”ከዚህ በላይ ጊዜ የሚፈጅበት ሊፈለግለት ጊዜ ስላሌለ ጊዜውን የጠበቀና ለአገራችን መፍትሄ ሊያስገኝ የሚችል ቪዥነሪ የሆነ አዋጅ እንደሆነ ውስጤ ስለሚሰማኝ ነው”

“አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም አገራችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከጨለማው ምዕራፍ ወደ ብርሃን በማሻገር ለአዲስ የመጣበት ቤዚክ ሞቲቩ እኔ አፕሪሼት የማደርገው ነው የተከበሩ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እኔም በአጋጣሚ ሆኖ በህዝባዊ መድረኮች የመገኘት እድሉን አግኝቼ ነበር እዛ ሲነሱ የነበሩ ሃሳቦችን ለማካተት የህዝብ አስተያየትና ድምጽ ለማክበር የተሄደበትን ርቀት ቋሚ ኮሚቴውንም አፕሪሼት ማድረግ እፈልጋለሁ”

“ይሄ አዋጅ ከመጽደቁ ጋር ተያይዞ በርግጥ ጦርነት ላይ ነን ሙሉ ለሙሉ አልቋጨንም አሁንም ትንኮሳዎች አሉ ቢኖሮም ትንኮሳዎች እንደ አገር እንደ ኢትዮጵያውያን አንድ መሆን መመካከር መነጋገር ለጋራ የአገር ጉዳይ ወደ አንድ ሃሳብ መምጣት በጣም ኢትዮጵያን ነው የሚጠቅመው ኢትዮያውያንን ነው የሚጠቅመው ለዚህ ደግሞ ይህ አዋጅ መጽደቅ ጉልበት ነው የሚሆነው”

ለህዝብ ግልጽ ለማድረግ እንዲቻል በውይይቱ የሚሳተፉ አካላት በግልጽ እንዲቀመጡም የምክር ቤት አባላት ሐሳብ አንስተዋል።

በተነሱ ሐሳቦች ላይ ማብራሪያ የሰጡት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ መንግስቱ አዋጁ በአጠቃላይ በአገሪቱ በህዝብ ተሳትፎ የሚደረግ ምክክር እንደሆነ እንጂ የቡድኖች ጉዳይ አልደነገገም ብለዋል።

የአዋጁ ዓላማ ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው ጉዳይ መክረው መፍትሔ እንዲያስቀምጡ የሚያስችል መሆኑንም አክለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ ገለልተኛ በሆነ መንገድ እንዲቋቋም ግልጽ፣ አሳታፊና አካታች በሆነ መንገድ ይመራል ብለዋል።

አገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ከማቋቋምና ምክክሩን ከማድረግ ጎን ለጎን በጦርነቱ የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው መመለስና ማቋቋም እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎችን መልሶ መገንባት ትኩረት እንዲሰጠው የምክር ቤት አባላት አስገንዝበዋል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ በተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ ምክር ቤቱ የአዋጁን አስፈላጊነትና ወቅታዊነት መርምሮ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።