እንደ ጀማል ትኩዬ ያሉ የበርካታ ተስፈኛ ወጣቶችን ጉዞ በአጭር ያስቀረው አሸባሪው ህወሃት”

191

ወጣት ጀማል ትኩዬ በ20ዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኝ መርሳ ከተማ ተወልዶ ያደገ ወጣት ነው።

ጀማል ጨዋታ አዋቂና ስራ ወዳድ መሆኑን የሚያውቁት ሁሉ ይናገሩለታል፤ ይመሰክሩታል።

ትዳር ከመሰረተ አንድ ዓመት እንኳ በቅጡ ያላጣጣመው ወጣት ጀማል ዐይኑን በዐይኑ ለማየት ጥቂት ጊዜ ነበር የቀሩት።ጀማል የራሱን አዲስ ጎጆ ለመምራትና አቅመ ደካማ የሆኑት እናትና አባቱን ለመደገፍ ሲል ቀን ከሌት በስራ ይታትራል።

ስለ ጀማል የሚያውቁት ሲናገሩ አቅመ ደካማ እናትና አባቱን ለማገዝ ሲል ከእረፍት ይልቅ ብዙ ጊዜውን በስራ ያሳልፋል ይላሉ።

ጀማል ጥሮ ግሮ ለፍቶና ታትሮ ባገኛት ጥቂት ገንዘብ ቤተሰቦቹን ለማስተዳደርና ለመደገፍ ይረዳው ዘንድ አዲስ በገዛት ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ በሚያገኘው ገቢ ቤተሰቡን ያስተዳድራል፤ ይደግፋል።

የቤተሰቡ አለኝታ የሆነው ጀማል ህይወትን ለማሸነፍ ሲል ጠንክሮ በመስራት ነገን ለማሸነፍ ተስፋን ሰንቆ ይጓዝ ነበር።

ሩቅ ዓላሚው ጀማል ህልሙና ጉዞ ዛሬ ላይ በአሸባሪው ህወሓት አማካኝነት እስከወዲያኛው ላይመለስ አብሮት አሸልቧል።

ነገሩ የሆነው እንዲህ ነው፤ መርሳ ከተማ በአሸባሪው ህወሓት እጅ በወደቀችበት ጊዜ የሽብር ቡድኑ በከተማ ከፍተኛ ሰቆቃና ግፍ በነዋሪዎቿ ላይ እያደረሰ ነበር።

ታዲያ ነዋሪዎቹ በሽብር ቡድኑ የሚደርስባቸውን ስቃይና በደል በራቸውን ዘግተው በርሃብ እና ውሃ ጥም የሚቋቋሙት ባለመሆኑ የእለት እንጀራቸውን ለማግኘት ሲሉ ሞትን ተጋፍጠው ስራቸውን ያከናውናሉ።

ጀማልም ልክ እንደ ሌሎቹ የመርሳ ከተማ ነዋሪዎች ሁሉ የእሱን እጅ የሚጠበቁ ወላጆቹን እና ትዳሩን ከረሃብና ውሃ ጥም ለመታደግ ሲል የእለት እንጀራውን ለማግኘት በመዳከር ሳለ ነበር በሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች እጅ የገባው።

እንደወትሮው ሁሉ ባጃጁን አፀዳድቶና አሰናድቶ ዐይኑን በዐይኑ ልታሳየው ቀኗ የተቃረበ ባለቤቱን “ሰላም ዋይልኝ” ብሎ ነበር ከቤቱ ማልዶ የወጣው።

የመርሳ ከተማን ዋና አውራ ጎዳና ይዞ ተሳፋሪ ፍለጋ በማማተር ላይ ሳለ በድንገት የአሸባሪው ታጣቂዎች አይን ውስጥ ገባ።

የአሸባሪው ቡድን ሶስት ታጣቂዎች ጀማልን አስቁመው ከመቅፅበት ወደ ባጃጇ መግባታቸውን የአይን እማኞች ይገልጻሉ።

እንደዘበት ከቤቱ ወጥቶ መመለስን ሲያስብ የነበረው ጀማል በአሸባሪዎቹ ተጠልፎ 45 ኪሎ ሜትር ተጉዞ ወልዲያን አልፎ አልወሃ በሚባለው አካባቢ ደረሰ።

እዚህ ቦታ ላይ አሸባሪዎች በጀማል ህይወት ላይ ወሰኑበት፤ ልብሱን አስወልቀው በውስጥ ልብስ ብቻ ካስቀሩት በኋላ በክላሽ ደጋግመው በመተኮስ ገድለውት ባጃጇን ይዘው ጠፉ።

ይህንን ድርጊት በድብቅና በርቀት ሆነው ይከታተሉ የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች የጀማልን አስከሬን ከወደቀበት ሄደው አነሱ።ጀማል ጭካኔ በተሞላበት ግዲያ ህይወቱ በማለፉ የአካባቢው ነዋሪዎች በአቅራቢያው ተጥሎ ያገኙትን መታወቂያ በመያዝ ሞቱን ለቤተሰቡ ለማርዳት ተነጋግረው ይወስናሉ።

በአድራሻው መሰረት መርሳ በመገኘትም ለጀማል ቤተሰቦች ሞቱን በማርዳት አስከሬኑ ያለበት ቦታ ድረስ ይዘዋቸው ሄደዋል። የጀማልን ሞት በተመለከተ የኢዜአ ሪፖርተር መርሳ ከተማ በመገኘት ያነጋገራት ባለቤቱ ሰሚራ ይመር “ የባለቤቴ ሞት መሪር ሀዘንም የከፋ ችግርም ላይ ጥሎኛል” ትላለች።

የጀማል ሞት እኔን ጨምሮ አቅመ ደካማ እናትና አባቱን ለከባድ ሃዘንና የከፋ ችግር ዳርጎናል የምትለው ሰሚራ፤ ዐይኑን በዐይኑ ለማየት ቀናቶችን በጉጉት ሲጠባበቅ የነበረውን ባለቤቴን በአሸባሪው ህወሃት ተነጥቄያለሁ ብላለች።

“አሸባሪዎቹ ባጃጇን ለመውሰድ ሲሉ አትግደሉኝ ውሰዷት እያለ ቢለምናቸውም በጭካኔ ገደሉት” በማለት መራር ሃዘንና የከፋ ችግር ውስጥ መሆኗን አክላ ገልፃለች።

አሸባሪዎቹ ጀማልን ሲገድሉ በድብቅ የተመለከቱ ሰዎች መታወቂያውን በማግኘታቸው በአድራሻው መሠረት ተገኝተው ሞቱን ተረድተን አስከሬንኑንም ማግኘታቸውን ተናግራለች።

ከጀማል ሞት በኋላ ሁለት ሳምንታት ቆይታ ሴት ልጅ በሰላም መገላገሏን የተናገረችው ሰሚራ “ ሃዘኑ እንደ እግር እሳት እያንገበገበኝ፤ በችግር ውስጥ ወልጄ ተኝቼ የእለት ጉርስ የማጣበት ጊዜ በዝቷል” ትላለች።

“ወላጅ እናቴን በህጻንነቴ በሞት ተነጥቄያለው፤ አሁን ያለሁት ደካማ ሴት አያቴን ተጠግቼ ነው፤ በመሆኑም የእኔም የህፃኗም ህይወት አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ይገኛል” በማለት ሲቃ በተናነቀው ድምጿ የሌሎችን ድጋፍ ጠይቃለች።

የሰሚራ አያት ወይዘሮ ሊዝን ሙሃመድ አሊ፤ እሳቸው ባላቸው አቅም ሁሉ ለማገዝ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም ካላቸው የአቅም ውስንነት የተነሳ መቸገራቸውን አልደበቁም።

አሸባሪው ህወሃት በወረራ በቆየባቸው አማራ እና አፋር ክልሎች ከዘረፋና ውድመት በተጨማሪ እንደ ጀማል ትኩዬ ያሉ የበርካታ ተስፈኛ ወጣቶችን ጉዞ በአጭር አስቀርቷል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️