ተዘዋዋሪ ችሎቱ በ194 ሰዎች ሞት ወንጀል በተከሰሱ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላለፈ

97

አሶሳ ፤ ታህሳስ 20 / 2014(ኢዜአ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አሶሳ እና አካባቢው አንደኛ ተዘዋዋሪ ችሎት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን ካማሽ ወረዳ በ194 ሰዎች ሞት እና 27 ሚሊዮን ብር በሚገመት ንብረት ውድመት ወንጀል ከተከሰሱ 21 ሰዎች መካከል በ10ሩ ላይ የጥፋኝት ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

ችሎቱ የጥፋተኝነት ውሳኔውን ያሳለፈው  በእነ ጸጋዬ ተሰማ የክስ መዝገብ ክስ የቀረበባቸው ላይ ነው፡፡

በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ አቃቢ ህግ ዘርፍ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጸው፤ በካማሽ ወረዳ ከመስከረም 16 / 2011 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም. ግጭት ተከስቶ ነበር፡፡

በግጭቱ 194 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በርካታ ሰዎች ከአካባቢው መፈናቀላቸውንና  በግጭቱ 27 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን  አስታውቋል፡፡

ወንጀሉ የተፈጸመው በጦር መሳሪያ እና በስለታም መሳሪያዎች ጭምር እንደሆነ አመልክቷል፡፡

ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ የፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ አቃቢ ህግ ዘርፍ በእነጸጋዬ ተሰማ የክስ መዝገብ በ21 ሰዎች ላይ የእርሰ በርስ ጦርነት በማስነሳት፣ በመሳተፍ እና በከባድ የግድያ ወንጀል ክስ መመስረቱን ተገልጿል፡፡

የቀረበባቸውን ክስ በማረሚያ ቤት ሆነው  በጊዜ ቀጠሮ ሲከታተሉ ከነበሩ ከእነኚሁ 21 ተከሳሾች መካከል የጠቅላይ አቃቢ ህግ ዘርፍ በአስሩ ላይ ከ30 በላይ የሰው ምስክሮች እና የሰነድ ማስረጃ ማቅረቡ ተመልከቷል፡፡

አስሩ ግለሰቦች በክስ መዝገቡ የቀረበባቸውን ማስረጃ መከላከል ባለመቻላቸው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አሶሳ እና አካባቢው አንደኛ ተዘዋዋሪ ችሎት ዛሬ በአሶሳ ከተማ በዋለው ችሎት የጥፋተኝነት ውሳኔ ማሳተላለፉን  የጠቅላይ አቃቢ ህግ ዘርፍ አመልክቷል፡፡

ቀሪ 11 ተከሳሾች ደግሞ የአቃቢ ህግ የሰው ምስክሮች ባለመቅረባቸው ምክንያት ከክሱ ነጻ የወጡ እና ክሳቸው ለጊዜው የተቋረጠባቸው እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

ጥፋተኛ የተባሉ ተከሳሾች ወንጀሉ የፈጸሙት ጉዳያቸው በሌላ የወንጀል ክስ መዝገብ እየታዬ ከሚገኝ ሌሎች 210 ሰዎች ጋር በመተባበር እንደሆነ የጠቅላይ አቃቢ ህግ ዘርፍ አስታውቋል፡፡  

ተዘዋዋሪ ችሎቱ ጥፋተኛ በተባሉ አስር ሰዎች ላይ ቅጣት ለመወሰን ለጥር 19 / 2014 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ተመልክቷል፡፡

በዚሁ የተለዋጭ ቀጠሮ ዕለት የተከሳሾች ጠበቆች የቅጣት ማቅለያ እንዲሁም አቃቢ ህግ የቅጣት ማክበጃ ካላቸው እንዲያቀርቡ ተዘዋዋሪ ችሎቱ አዟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም