ኢጋድ በድንበር አካባቢዎች የኮሮና እና ሌሎች ወረርሽኞችን ለመከላከል የሚውል 60 ሚሊዮን ዩሮ መመደቡን አስታወቀ

ጎንደር፤ ታህሳስ 20/2014 (ኢዜአ) በድንበር አካባቢዎች የኮሮና ቫይረስ እና ሌሎች ወረርሽኞችን ለመከላከል 60 ሚሊዮን ዩሮ መድቦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) አስታወቀ።

ድርጅቱ ኮሮናን ጨምሮ ድንበር ዘለል የወረርሽኝ በሽታዎችን መከላከልና መቆጣጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በጎንደር ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በኢጋድ የኮቪድ-19 ምላሽ ዋና አስተባባሪ ዶክተር ግሩም ሃይሉ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ድንበር ተሻጋሪ በሽታዎችን ለመከላከል ለሚከናወኑ  ሥራዎች የተመደበው ገንዘብ  ከአውሮፓ ሕብረት የተገኘ ድጋፍ ነው።

ገንዘቡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ የድርጅቱ አባል ሀገራት የኮሮና ቫይረስና ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ቅንጅታዊ አሰራርን እንዲያዳብሩ የሚያስችላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

አባል ሀገራቱ በድንበር አካባቢ ኮሮናን በመከላከልና በመቆጣጠር 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ህዝብ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ እያደረጉ መሆኑንም ዶክተር ግሩም አመልክተዋል፡፡  

በኢትዮጵያም በአፋር፣ በሞያሌና በመተማ አካባቢዎች ከአጎራባች ሀገራት ጋር በሚካሄድ የንግድ እንቅስቃሴ የኮሮና  ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ ከአቅም ግንባታ በተጨማሪ የመከላከያ ግብአቶች ድጋፍ መደረጉን ነው ያስረዱት፡፡

የምክክር  መድረኩ ዓላማም አባል ሀገራት በድንበር አካባቢ ጠንካራ የመረጃ ልውውጥና የመደጋገፍ ባህል በማሳደግ ለወረርሽኙ የሚሰጡትን ምላሽ ማጠናከር መሆኑንም ዶክተር ግሩም ገልጸዋል።

"በመተማ አካባቢ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መጀመሪያ ላይ የተደረገው እንቅስቃሴ የተጠናከረ ነበር" ያሉት ደግሞ የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ  ወይዘሮ ክሽን ወልዴ ናቸው።

በዞኑ በድንበር አካባቢ ባሉ የመግቢያና መውጫ በሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ዜጎች የኮሮና ምርመራ እንዲያካሄዱ ማድረግን ጨምሮ ተጠርጣዎችን ለይቶ ወደ ማቆያ እንዲገቡ ሲደረግ እንደነበር አስታውሰዋል።

"ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መዘናጋት በመፈጠሩ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሲሰራ የነበረው ሥራ እየተቀዛቀዘ መጥቷል" ብለዋል።

የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በማድረግ፣ እጆችን በመታጠብና አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል እንደሚሰራም ሃላፊዋ ተናገረዋል።

ኢጋድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችለውን የጋራ ስምምነት ማድረጋቸውም ተመልክቷል።

ለሁለት ቀናት በቆየው የምክክር መድረኩ ላይ  የጤና ባለሙያዎችና የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም