በመዲናዋ የኮቪድ 19 መመሪያን በማይተገብሩ የምግብና መጠጥ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ እርምጃ ይወሰዳል

81

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20/2014(ኢዜአ) በመዲናዋ የኮቪድ 19 መመሪያን በማይተገብሩ የምግብና መጠጥ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የአዲስ አበባ ምግብ፣ መድሃኒት፣ ጤና ክብካቤ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ገለፀ፡፡

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ህብረተሰብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ቫይረሱን ለመከላከል የጥንቃቄ ተግባራት በስፋት ሲከናወኑ እንደነበር ይታወሳል።

በተለይ በምግብ ቤቶችና መጠጥ ቤቶች ውስጥ በአንድ ጠረጴዛ ከሶስት ሰው በላይ እንዳይቀመጥ በመመሪያ መከልከሉ ይታወቃል።

ህብረተሰቡም እጁን በተደጋጋሚ በመታጠብ፣ የእጅ ማፅጃ ኬሚካል በመጠቀም እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በማድረግ የጤና መመሪያውን ሲተገብር እንደነበር አይዘነጋም።

ሆኖም የቫይረሱ ስርጭት እየቀነሰ ነው በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ህብረተሰቡ ሲያደርጋቸው የነበሩ ጥንቃቄዎችን ወደ ጎን ማለቱ አሁን ላይ ዋጋ ማስከፈል ጀምሯል።

በኢትዮጵያ ትናንት በተደረገ 13 ሺህ 280 የላቦራቶሪ ናሙና ምርመራ 5 ሺህ 185 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል፤ ይህም አሁን ላይ ወረረሽኙ የደረሰበትን ደረጃ በግልጽ ያሳያል፡፡

የአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት በዳዳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የምግብና መጠጥ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የጥንቃቄ መመሪያን በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ እያደረጉ አይደለም፡፡

በአሁኑ ወቅት ጉዳዩን በሚመለከት በህብረተሰቡና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ከፍተኛ መዘናጋት መስተዋሉንም አንስተዋል።

ባለስልጣኑም በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ሲያደርግ የነበረው ቁጥጥር መላላቱንም ነው የተናገሩት፡፡

ተቋማቱ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ አክብረው እንዲሰሩ ባለስልጣኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል።

በተያዘው ዓመት 16 ሺህ ለሚደርሱ ተቋማት በሶስት ዙር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል፡፡

አሁን ላይ ወረርሽኙ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ በዘመቻ መልክ ሁሉንም ተቋማት የማስገንዘብ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ባለስልጣኑ ከማስተማር ባሻገር በቀጣይ የኮቪድ 19 መመሪያን በማይተገብሩ ተቋማት ላይ እርምጃዎችን እንደሚወስድም ነው ያስጠነቀቁት።

ህብረተሰቡ ለራሱ ጤና ራሱ ዘብ በመሆን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንዲከላከልም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም