በዳንጉር ወረዳ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለመከላከያ ሰራዊት ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

99

ግልገል በለስ፤ ታህሳስ 20/2014(ኢዜአ) በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ክንፉ እንደገለጹት ገንዘቡን የለገሱት ነጋዴዎች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው ብለዋል።

ድጋፉ በመተከል ዞን የህግ የበላይነትን ለማስከበር ተሰማርተው ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የየክልሉ ልዩ ሃይሎች እንደሚውል አመልክተው፤ ከተለገሰው ገንዝብ ውስጥ ከ900 ሺህ ብር በላይ ወጭ በማድረግ 30 ሰንጋ በሬዎችን ማበርከታቸውን ጠቅሰዋል።

ሰራዊቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር እየከፈለ ያለውን መስዋዕትነት በመረዳት እና የተጀመረው ሰላም የማስከበር ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማገዝ የተደረገ ድጋፍ እንደሆነ ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

የወረዳው ህዝብ የመተከልን ሰላም ለመመለስ ሁሉን አቀፍ ተግባራት ሲያከናውን መቆየቱን አውስተው፤ አሁንም ሰራዊቱ የጀመረውን ሀገርን የማዳን ተግባር ለማጠናከር የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

በድጋፍ ርክክቡ ላይ የተገኙት ኮሎኔል በስፋት ፈንቴ በበኩላቸው፤ ድጋፉ የሰራዊቱን ሞራልና አቅም በማሳደግ የተጀመረው ህግ የማስከበር ስራ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የአሸባሪው ህወሃትን አጀንዳ ተቀብለው ቀጠናውን ለማወክ የሚሞክሩ ጸረ ሰላም ሃይሎችን ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ሰራዊቱ በሙሉ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የወረዳው ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ የኢትዮዽያን አንድነት ለማስከበር የሚያደርጉትን ሁሉ አቀፍ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በወረዳው እስካሁን ከ3 ነጥብ 1ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተሰብስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም