የንግዱ ማህበረሰብ የወደሙ ተቋማትን መልሶ በማቋቋምና በሰላም ግንባታ ላይ የሚጠበቅበትን ሚና ሊወጣ ይገባል

63

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 20/2014(ኢዜአ) የንግዱ ማህበረሰብ የወደሙ ተቋማትን መልሶ በማቋቋምና በሰላም ግንባታ ሂደት ላይ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ የሰላም ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

"ንግድ ለሰላምና ለዘላቂ የኢትዮጵያ ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ በሰላም ሚኒስቴር እና ኢኖቬቲቭ አፍሪካ የተሰኘ ድርጅት በጋራ ያዘጋጁት ውይይት ተካሒዷል።

በመድረኩ ከ150 የሚበልጡ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል።

የንግዱ ማህበረሰብ በህዝቦች ትስስርና ሰላማዊ ግንኙነት ላይ ጉልህ ሚና እንዳለው በመገንዘብ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ተጠይቋል።

የንግድ ተቋማት በማህበረሰብ የሰላም ግንባታ ስራዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ራሳቸውም ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉም ነው በውይይቱ የተነሳው፡፡

በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ዳይሬክተር ወይዘሮ አስማ ረዲ፤ የንግዱ ማህበረሰብ በስራው ሀገሩን የሚያስብና የሚያስቀድም መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

በሰላም ግንባታ ሒደት ውስጥ የሚጠበቅበትን ሚና መወጣት እንዳለበትም እንዲሁ።

በሚኒስቴሩ የስትራቴጂክ አጋርነት እና ተጠሪ ተቋማት ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ሻንቆ ደሳለኝ በበኩላቸው፤ የንግዱ ማህበረሰብ ውስጣዊ ሰላሙን በማስጠበቅ ሀገር ግንባታ የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል።

በተለይም ህጋዊነትን ምሰሶ በማድረግ ሊሰራ እንደሚገባ እና ሀገር ፈተና በወደቀችበት ጊዜም ይህን ይበልጥ ታሳቢ ባደረገ መልኩ መንቀሳቀስ አለበት ነው ያሉት፡፡

የንግድ ስራን በውጤታማነት ለማከናወን ሰላም ወሳኝ ሚና እንዳለው የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ምክር ቤት የምርምርና አድቮኬሲ ዳይሬክተር አቶ ሚሊዮን ፈለቀ ናቸው፡፡

የንግዱ ማህበረሰብ ለሰላም ግንባታና በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ በመገንባት ረገድ ሚናውን መወጣት እንደሚጠበቅበት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም