ከአሜሪካ አሉታዊ ፖሊሲ ጀርባ እነማን አሉ?

500

ኢትዮጵያና አሜሪካ ለ120 ዓመታት ገደማ የዘለቀ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመፍጠር በጋራ መስራት የቻሉ አገራት ናቸው። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን አሜሪካ በኢትዮጵያ እየተከተለች ያለው ፖሊሲ ከገንቢነቱ ይልቅ አፍራሽና አደገኛ እየሆነ መጥቷል። 

አሜሪካ ኢትዮጵያን አስመልክታ እየተከተለች ያለው ስሁት ገንቢ ያልሆነ ፖሊሲ የሁለቱን አገራት የቆየ ወዳጅነትና ትብብር እየጎዳው መሆኑን በግልጽ እየታየ ነው። ለዚህም ነው አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የባይደን አስተዳደር በተሳሳተ ፖሊሲ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነትን በመቃወም “እጃቹሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ (Hands Off)” እና “#በቃ (#No More)” ሲሉ ተቃውሟቸውን በማሰማት ላይ የሚገኙት።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከ110 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላትና ከዚህ ውስጥ የበዛው የተማረና ወጣት መሆኑ ደግሞ በፍጥነት እያደገ ካለው ፖለቲካዊ ለውጥና ኢኮኖሚዋ እመርታ ጋር ተዳምሮ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ይበልጥ ተፈላጊነቷን የሚያጎላው ነው።

ሃቁ ይህ ሆኖ ሳለ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በነጩ ቤተ-መንግሥትና በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ሥልጣን የተቆናጠጡ ጥቂት ግለሰቦች በኢትዮጵያና አፍሪካ ጉዳዮች ተጽዕኖ ሲያሳድሩ ተስተውለዋል።  

ኢትዮጵያን ጨምሮ አሜሪካ በአፍሪካ ከምትከተለው አፍራሽና የተሳሰተ ፖሊሲ ጀርባ ያሉ ተዋናዮች እነማን እንደሆኑ የኢንተለጀንስ ዕውነታን በማጣቀስ እንደሚከተለው ቀርቧል:-

ጌይል ስሚዝ (Gayle Smith)

የጌይል ስሚዝ እና የአሸባሪው ህዋሓት ቡድን ወዳጅነት በ1970ዎቹ እንደተጀመረ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ ደግሞ ጌይል በ1970 መገባደጃ ላይ በአፍሪካ ቀንድ የጋዜጠኝነት ሙያዋን በፍሪላንሰርነት በጀመረችበት ጊዜ መሆኑ ነው። ጌይል ስሚዝ ስለ ህወሓት-ወያኔ ዘገባዎችን ጽፋ በታላላቅ ዓለም አቀፍ ጋዜጦች ላይ ማስነበብ እስክትጀምር ድረስ ቡዱኑን ዓለም አያውቀውም ነበር።

በጋዜጠኝነት ካባ የተጀመረው የጌይል ስሚዝና የአሸባሪው ቡድን ጋብቻ አሁን ድረስ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላይ ጫና ለማሳደር እያገለገለ ይገኛል። ጌይል ስሚዝ እኤአ በየካቲት 1981 በክርስቲያን ሳይንስ ሞኒተር ጋዜጣ በፃፈችው ዘገባ የህወሓት ትልቁ ችግር የውጭ ድጋፍ እጦት በመሆኑ የቡድኑን ፈጣን ግስጋሴን መደገፍ ይገባል ስትል ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንዲያገኝ ቁልፍ ሚና ተጫውታለች።

በተመሳሳይ እኤአ በየካቲት 1981 በ ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ በፃፈችው ዘገባ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ መንግሥት ጫና እንዲያደርግና ተቃዋሚዎች አገዛዙን ለማስወገድ የሚያደርጉትን ጥረት እንዲደግፍ ስትሰራ ነበር። በተለይ የህወሓት የሽምቅ ውጊያ በጣም ፈጣን ዕድገት ያለው ፀረ-መንግሥት እንቅስቃሴ እንደሆነ በመግለጽ ህወሓት ለአዲስ አበባ መንግሥት ቀጥተኛ ስጋት እየሆነ በመምጣቱ ድጋፍ ሊያገኝ ይገባዋል የሚሉ ዘገባዎችን በግዙፍና ተነባቢ ጋዜጦች በማውጣት ስታግዝ ቆይታለች።

ጌይል በዚህም አልተገታችም። እ.ኤ.አ. በ1990 ባወጣችው ጽሁፍ አሸባሪው ህወሓት 10 ምዕራባውያን ዜጎች ማፈኑን ተከላክላለች። ጌይል ስሚዝ ከሙያዊ አጋርነት ባለፈ የማነ ኪዳኔ ከሚባል የአሸባሪው ህወሓት ቡድን አባል ያልተገባ ግንኙነት እስከ መፍጠር ደርሳለች። በዚህም አላበቃች።

በዋሽንግተን ዲ.ሲ የተመሰረተው የትግራይ መረዳጃ ማህበር (Relief Society of Tigray-ReST) አማካሪ እና አስተባባሪም ነበረች። በትግርኛ ምህፃረ ቃሉ ማረት በሚል የሚጠራው ይኸው ድርጅት የህወሓት ሰብዓዊ ክንድ በመሆን ሲያገለግል ቆይቷል።

እ.ኤ.አ. በ2010 ለዕይታ የበቃው የቢቢሲ ዘጋቢ ፊልም ማረት በ1980ዎቹ በዕርዳታ ያገኘውን 11 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ስልታዊ በሆነ መልኩ የጦር መሳሪያ ግዢ ይፈጽምበት እንደነበር አጋልጧል። እንግዲህ ጌይል ስሚዝ ትመራው የነበረው ይህን ወንጀለኛ ድርጅትን ነበር ማለት ነው። (የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሥርዓተ ቀብር ላይ ጌይል ስሚዝ ያሰማቸው የመወድስ ንግግር ሳይዘነጋ)  

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በቅርቡ በሦስት የአፍሪካ አገራት ያልተሳካ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ጋኤል ስሚዝ በልዑካን ቡድኑ ውስጥ ተካተው ነበር (አሁን የጌይል ስሚዝ በዕድሜ መግፋት ልብ ይባልና በአንቱታ ይገለጹ)። ከ110 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን አሸባሪውን ህወሓት አንፈልግም በሚሉበት በዚህ ወቅት በኬንያ ጉብኝታቸው የኢትዮጵያ ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳ ነበር። አሁን ላይ ጌይል ስሚዝ በባይደን አስተዳደር የፕሬዝዳንቱ ልዩ ረዳት ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።                            

ሱዛን ራይስ (Susan Rice)

ሱዛን ኤልሳቤት ራይስ በክሊንተን አስተዳደር ዘመን የፕሬዝዳንቱ ልዩ ረዳት ሆነው የፖለቲካ ህይወታቸውን አሃዱ ማለታቸውን ነው ግለ ታሪካቸው የሚያስረዳው። ሱዛን ራይስ እ.ኤ.አ. ከ1993 እስከ 1997 በፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ሰራተኛ በመሆን አገልግለዋል። ከ1997 እስከ 2001 በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ፀሃፊ በመሆን የሰሩ ሲሆን አሜሪካዊቷ ዲፕሎማት የፖሊሲ አማካሪ እና እኤአ ከ2021 ጀምሮ የዩናይትድ ስቴትስ የሀገር ውስጥ ፖሊሲ ምክር ቤት ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በ2009 በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል።

እኤአ ከ2001 እስከ 2002 ደግሞ የኢንቴልሊብሪጅ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ማገልገል ችለዋል። ኢንቴልሊብሪጅ በዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ከአፍሪካ መንግሥታት ጋር የሚሰራ የስትራቴጂክ ትንታኔ ድርጅት ሲሆን ሱዛን ራይስ እና ጌይል ስሚዝ የዚህ ድርጅት ሰራተኞች ነበሩ። ጌይል ስሚዝ እና ሱዛን ራይስ የኢንተሊብሪጅ አገልግሎቶችን ለአፍሪካ መንግሥታት በመሸጥ እንደሚታወቁ የድርጅቱ የቀድሞ ሰራተኛ የነበረው ሃሚልተን ቢን ያስረዳል።

ሱዛን ራይስ በአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ጸሃፊነት ዘመናቸው የረባ ነገር ሳይፈይዱ ከማሳለፋቸው ባሻገር በዲፕሎማትነት ታሪካቸው ጥቁር አሻራ ጥለው በማለፍ ይታወቃሉ። የ 800 ሺህ ሩዋንዳውያን ህይወት የቀጠፈው የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለማስቆም ምንም ጥረት አለማድረጋቸው ደግሞ አሁን ድረስ ይወቀሳሉ። ሱዛን ራይስ ድርጊቱን ኮንነው የ ‘ዘር ማጥፋት’ የሚለውን ቃል ለመጠቀም እምቢተኛ በመሆናቸው አፍሪካውያን መቼም ይቅር የማይሉት ህፀጽ ሰርተዋል።

ሱዛን ራይስ እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ጸሃፊ ሆነው ሲያገለግሉ በህወሓት የሚመራውን መንግሥትን በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። እስከ መጨረሻው ድረስ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የቅርብ ወዳጅ ሆነውም ዘልቀዋል። የክሊንተን አስተዳደርም መለስ ዜናዊን ከአዲሱ የአፍሪካ መሪዎች መካከል አንዱ አድርጎ ሲሰይም ትልቅ ሚና ነበራቸው። (በመለስ ዜናዊ ሥርዓተ ቀብር ላይ እንደ ጌይል ስሚዝ ሁሉ ያሰሙት የመወድስ ንግግር ልብ ይሏል)  

በወቅቱ ወያኔ  መራሹ የኢሕአዴግ መንግሥት የሚካሄዳቸው ምርጫዎችን በማወደስ ሱዛን ራይስን የሚስተካከላቸው አልነበረም። በኢትዮጵያ የተካሄደው ምርጫ ዴሞክራሲዊነት አስመልክቶ ከጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ “መቶ በመቶ” ዴሞክራሲያዊ ነው በሚል ነበር በማፌዝ የመለሱት።

በኮንጎ ሚሊዮኖች በአሸባሪ ታጣቂዎች ሲገደሉ ሱዛን ራይስ ድርጊቱን ለማውገዝ አልፈቀዱም። ምክንያቱ ደግሞ አሸባሪው ቡድን የራይዝ ወዳጅ በሆኑት የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት የሚደገፉ በመሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ከወዳጃቸው ጋር የጥቅም ግጭት ውስጥ የሚያስገባቸው ሆኖ ስላገኙት ነው ማውገዝ የተሳናቸው ይላል የቀድሞ የአሜሪካ ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት ወኪል የነበረውና አሁን ላይ የፖለቲካ አክቲቪስት የሆነው ሬይሞንድ ማክገቨርን።

ሱዛን ራይስ በፀጥታው ምክር ቤት አምባሳደርነታቸው ዘመን በኢራን እና በሰሜን ኮሪያ ላይ ጠንካራ ማዕቀቦች እንዲጣሉ ግፊት ማድረግ ችለዋል። እኤአ በ2011 አሜሪካና የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (NATO) ሊቢያ ውስጥ ጣልቃ እንዲገቡ ሞግተዋል። ውጤቱ ደግሞ ያው አሁን የምናያትን የሲኦል ምድር ሊቢያን ፈጥረዋል። አፍቃሪ ህወሓት የሆኑት ራይስ በባይደን አስተዳደር ውስጥ የአገር ውስጥ ፖሊሲ ምክር ቤት ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል በኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ላይ ጫና መፍጠራቸውን ቀጥለዋል።

ዌንዲ ሩት ሼርማን (Wendy Ruth Sherman)

የ72 ዓመት አዛውንቷ ዌንዲ ሩት ሼርማን ካለፈው ዓመት ጀምሮ የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በማገለገል ላይ የሚገኙ አሜሪካዊት ፕሮፌሰር እና ዲፕሎማት ናቸው። ዌንዲ ሼርማን ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ህወሓት-ወያኔ መራሹ የኢትዮጵያ አገዛዝን በማመስገን የሚታወቁ ናቸው። የአሜሪካ መንግሥት አሸባሪው የህወሓት ቡድንን አስመልክቶ ለሚከተለው ፖሊሲ የዌንዲ ሼርማን አስተዋጽኦ ላቅ ያለ ነው።

ጄፍሪ ዴቪድ ፌልትማን (Jeffery D. Feltman)

ጄፍሪ ዴቪድ ፌልትማን ካለፈው ሚያዚያ ጀምሮ የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙ ዲፕሎማት ናቸው። ቀደም ሲል የተባበሩት መንግሥታት የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሃፊ ሆነው አገልግለዋል። በዚህም ፌልትማን የተባበሩት መንግሥታት በዓለም አቀፍ ደረጃ ግጭቶችን ለመከላከል እና ለማቃለል የሚያደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የመቆጣጠር ሚና ነበራቸው።

ፌልትማን በቀደሙት ዓመታት ከህወሓት መሪ ከነበረው መለስ ዜናዊ ጋር የነበራቸው አደገኛ ቀረቤታ ማንም የሚረሳው አይደለም። በመለስ ዜናዊ ሥርዓተ ቀበር ላይ ፌልትማን ያሰሙት ንግግር ደግሞ የቅርበታቸው ጥግ የሚያሳይ ነበር። አሁን ደግሞ በባይድን አስተዳደር ለአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የበግ ለምድ ለብሰው አሸባሪውን ህወሓት እሽሩሩ ሲሉ ይስተዋላሉ።

ሳማንታ ጄን ፓወር (Samantha Jane Power) USAID 

የዘር ሀረጋቸው ከወደ አየርላንድ የሚመዘዘው አይሪሽ-አሜሪካዊት ምሁር ሳማንታ ጄን ፓወር አሁን ላይ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ አስተዳዳሪ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። (የአየርላንድ መንግሥት ኢትዮጵያን አስመልክቶ የሚከተለው አፍራሽ አካሄድ ዛይዘነጋ) ቀደም ሲል በተባበሩት መንግሥታት 28ኛው የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሆነው ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል። 

የፖሊቲኮ ድረ-ገጽ የ“USAID ከፍተኛ ባለሥልጣንን ጠቅሶ ባስነበበው ዘገባ እኤአ. ግንቦት 3 ቀን 2021 USAID መምራት በጀመሩበት ጊዜ ከድርጅቱ ሰራተኞች ጋር ባደረጉት የመጀመሪያ ውይይት ፓወር በትግራይ ክልል እና ከዚያም በላይ እየደረሰ ላለው አደጋ የኢትዮጵያ መንግሥት ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባት የማሸማቀቅ መንገዶችን እንዲያጤኑ ጠይቀዋል። የኃላፊነት መንበሩን ከተቆናጠጡ ወዲህ ደግሞ የአሸባሪው ህውሓት ቡድን በሰብዓዊ ድጋፍ ስም ያልተገባና የተለያዩ ድጋፎች እንዲያገኝ ከማድረጋቸው ሌላ የአሜሪካ መንግሥት የተሳሳተ ፖሊሲን በመፈጸም በኩል ጉልህ ድርሻ እያደረጉ ይገኛሉ። 

ጌይል ስሚዝ እና ሱዛን ራይስ ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጋር የነበራቸው የ40 ዓመታት ግንኙነት አሁን በሰሜን ኢትዮጵያ ለተፈጠረው ቀውስ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የሚያሳይ ነው። በኢትዮጵያና በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ አብዛኞቹ ያልተሳኩ እና የተሳሳቱ ፖሊሲዎች አሜሪካ እንድትከተል የእነዚህ ሰዎች ድርሻ ከፍ ያለ ነበር።   

በአሜሪካ መንግሥት ውስጥ ሚዛናዊ እና በአፍሪካ ጉዳዮች የተራቀቁ ባለሙያዎች አለመኖራቸው ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ በአፍሪካ ላይ ያላትን የረዥም ጊዜ ጥቅም እንዲናጋ እያደረገው ይገኛል። እንደ ጌይል ስሚዝ እና ሱዛን ራይስ ያሉ ከተከታታይ የአሜሪካ አስተዳደር ጋር ያላቸው ቅርርብ ተጠቅመው በአፍሪካ ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ የተሳሳተና ገንቢ ያልሆነ ብሎም ሚዛኑን የሳተ ፖሊሲን ፈጥሯል። የዩናትድ ስቴትስ ህዝብና መንግሥት የእነዚህን ግለሰቦች ሚና ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እና አሜሪካ በአፍሪካ ካላት የረጅም ጊዜ ወዳጅነትና ጥቅም አኳያ አጢነውና መዝነው ሊያርሙት ይገባል።