የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና የብሉ ናይል ግዛት አመራሮች ለህዝቦቻቸው ተጠቃሚነት እንደሚሰሩ አስታወቁ

79

አሶሳ ፤ ታህሳስ 20 / 2014(ኢዜአ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና በሱዳን የብሉ ናይል ግዛት አስተዳደር አመራሮች ግንኙነታቸውን በማጠናከር ለህዝቦቻቸው የበለጠ ተጠቃሚነት እንደሚሰሩ አስታወቁ፡፡

የክልሉና የግዛቱ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች  የተሳተፉበት በጋራ የድንበር ልማት ትብብር ላይ የተወያየ መድረክ ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በውይይቱ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ እና የሱዳን ህዝቦች ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት አላቸው፡፡

ባህል፣ ቋንቋ፣ አኗኗር እና ሌሎችንም እሴቶቻቸውን የጠቀሱት አቶ አሻድሊ ፤የአባይ ወንዝን ጨምሮ የተፈጥሮ ህብቶችንም በጋራ መጠቀም የሃገራቱን ህዝቦች ያስተሳሰረ ጉዳይ እንደሆነ አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በታሪኳ የሱዳን ህዝብን ተጠቃሚነት የሚቃረን መርህ ተከትላ እንደማታውቅ ጠቁመው፤ ከሃገራዊ ለውጥ በኋላ የጎረቤት ሃገራት የጋራ ጥቅም ላይ  የበለጠ ትኩረት መስጠቷን ጠቁመዋል፡፡

ሃገሪቱ ይህን የምትከተለው የኢትዮጵያና የሱዳን ሠላም ሲረጋገጥ እንደሆነ ስለምታምን መሆኑን ለስብሰባው ልኡካን አብራርተዋል፡፡

ሁለቱ ክልሉና ግዛቱ የሀገሮቻቸውን የውጪ ፖሊሲ መሠረት በማድረግ የጋራ ኮሚሽን በማቋቋም ህዝቦቻቸውን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም በጸጥታ ላይ  ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በሀገራቱ ውስጥ በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች ሳቢያ ግንኙነቱ መገደቡን ጠቁመው፤ በቀጣይ የተሻለ እቅድ በማዘጋጀት  ለመተገበር እንደሚሰራ አቶ አሻድሊ አስታውቀዋል፡፡

በተለይ በጋራ የድንበር አካባቢ ጸጥታን ማረጋገጥ ዋነኛ ትኩረት የሚሰጠው እንደሚሆን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡

በሱዳን የብሉ ናይል ግዛት ፕሬዚዳንት አህመድ አል-ኡምዳ ባዲ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሱዳን የፖለቲካ ልዩነቶችን በማጥበብ ሃገሪቱ ወደ ሠላማዊ ሽግግር እንድትመጣ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ልባዊ ምስጋና አቅርባለሁ ብለዋል፡፡

ይህ ውይይት  በኢትዮጵያ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና በሱዳን የብሉ ናይል ግዛት አስተዳደር  ህዝቦች ተጠቃሚ ለማድረግ ከዚህ ቀደም የጀመርናቸውን ጥረቶች በአዲሰ መልክ ለማጠናከር ያስችላል ብለዋል፡፡

የብሉ ናይል ግዛት አስተዳደር በሁለቱ አካባቢዎች  የሚገኙ  ተቃዋሚ ሃይሎችን ወደ ሠላማዊ ውይይት በማምጣት የሀገራቱን ሠላም ዘላቂ ማድረግ ትኩረት እንደሚሰጥ ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም ስደተኞችን የመመለስ ጉዳይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና የብሉ ናይል ግዛት አስተዳደር ከዚህ ቀደም  ያደረጓቸውን የጋራ ስምምነቶችን መሠረት አድረግን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

በተለይ የጸጥታ ጉዳይን ጨምሮ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ማህበራዊ፣ ቴክኖሎጂ እና ባህላዊ ጉዳዮችን ለማጠናከር ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር ቅንጅታዊ አሰራር መፍጠር ትኩረት እንሚሰጠው ፕሬዚዳንት አህመድ ገልጸዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና  የብሉ ናይል ግዛት አስተዳደር በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና በጸጥታ ላይ   በቀጣይ በሚሰሯቸው ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና የብሉ ናይል ግዛት አስተዳደር  ከፍተኛ አመራሮች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም