በመዲናዋ የሚንቀሳቀሱ 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች በአማራና አፋር ክልሎች የወደሙ አራት የማህበራዊ ተቋማትን ሊገነቡ ነው

145

አዲስ አበባ፣  ታህሳስ 20/2014(ኢዜአ) በአዲስ አበባ የሚንቀሳቀሱ 22 ፖለቲካ ፓርቲዎች በአማራ እና አፋር ክልሎች የወደሙ አራት የማህበራዊ ተቋማትን ሊገነቡ መሆኑን የፓርቲዎች ጥምረት ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስታወቀ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ተደቅኖ የነበረውን የሕልውና ስጋት ለመቀልበስ በተደረገው አገራዊ ዘመቻ ከመንግስትና ህዝብ ጎን ተሰልፈው የበኩላቸውን ሚና ሲወጡ ተስተውሏል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ 22 ፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረትም አገራዊ የሕልውና ስጋቱን ለመቀልበስ በሀብት ማሰባሰብ፣ ፕሮፓጋንዳ፣ ጸጥታና ደህንነት፣ በዘማች ምልመላና ሌሎች ተያያዥ ዘርፎች ላይ ሚናውን አበርክቷል።

በእያንዳንዱ ዘርፍ ኮሚቴ አዋቅሮ የወገንን ሃይል ሲደግፍ መቆየቱን የጥምረቱ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የኢሕአፓ ህዝብ ግንኙነት ኅላፊ መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት ለኢዜአ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በደሴ ግንባር በመገኘት ከ18 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ ለወገን ጥምር ጦር ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

በተጨማሪ አዲስ አበባ ቤላ ሆስፒታል ህክምና ላይ ለሚገኙ የሰራዊት አባላት የምግብና ህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር  ለሆስፒታሉ እድሳት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ቀጣዩ ግንባር ደግሞ ኢትዮጵያን ለምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት ከዳረገው ጦርነት በምታገግምበት አማራጮች ላይ መሳተፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሸባሪው የሕወሃት ወራሪ ሃይል በከፍተኛ ደረጃ የወደመው ተቋማትን መልሶ መገንባት እና በጦርነቱ ተፈናቅለው ለማህበራዊ ቀውስ የተዳረጉ ወገኖችን መደገፍ ቅድሚያ ይሰጠዋል ብለዋል።

በዚህም አዲስ አበባ የሚንቀሳቀሱ 22 ፓርቲዎች ጥምረት በአማራና አፋር ክልሎች በእያንዳንዳቸው አንድ ሆስፒታልና አንድ ትምህርት ቤት በድምሩ አራት ተቋማትን ሊያስገነባ መወሰኑን ገልጸዋል።

ፓርቲዎች፣ ፖለቲከኞች፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ያሉ የፓርቲ ደጋፊዎች የሀብት ማሰባሰብ እንቅስቃሴውን በብርቱ ደግፈው እያገዙ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

ፓርቲዎቹ አገር ከፖለቲካ ልዩነት እና ከፓርቲ በላይ ነው በሚል መርህ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ኢትዮጵያ እንደ አገር የገጠማትን ችግር እንድትሻገር ጉልህ ሚና አለው ነው ያሉት።

ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደበፊቱ አማራጭ ሀሳብ የሌላቸው የይስሙላ ፓርቲ ስብስብ ሳይሆኑ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋትና ለአገር የሚቆረቆሩ መሆናቸውን ማሳያ ነው ብለዋል።

ፓርቲዎች እና ደጋፊዎቻቸው ትብብር ተቋማቱን መልሶ ለመገንባት ጥረትን ማገዝ ከሚሹ ወገኖች ሀብት በማሰባሰብ በአጭር ጊዜ ተቋማቱን መልሶ ገንብቶ ለማስረከብ ጥምረቱ ይሰራል ነው ያሉት።

ፓርቲዎች አዲስ አበባ እስከ ወረዳ ድረስ ባላቸው መዋቅር የሀብት ማሰባሰብ ስራውን እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።