ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የኢትዮጵያውያንን አንድነትና ህብረት ያጠናክራል

65

ሆሳዕና፣ ታህሳስ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ ) ብሄራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር የኢትዮጵያውያንን አንድነትና ህብረት እንደሚያጠናክር የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም ገለጹ።

ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዙሪያ የሚያሰለጥናቸውን ከ2 ሺህ 200 በላይ ተማሪዎችን ዛሬ ተቀብሏል።

ሚኒስትሩ በስልጠናው ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት፤ መርሐ ግብሩ የኢትዮጵያን አንድነትና ህብረት በማጠናከር ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ ያግዛል።

ሰልጣኞቹ ስልጠናቸውን ሲያጠናቅቁ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተሰማርተው አገልግሎት እንደሚሰጡ አቶ ብናልፍ አስታውቀዋል።

በጎ ፈቃደኞቹ በሚሰማሩባቸው አካባቢዎች አዳዲስ ተሞክሮዎችን የሚቀስሙበትና ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጠናከር ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የገጠማት ፈተና ለበርካቶች መፈናቀልና ሞት ምክንያት መሆኑን የገለጹት አቶ ብናልፍ፤ መላው ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ በአንድነት ተንቀሳቅሶ የአገሪቱን ህልውና ማስጠበቅ መቻሉን ተናግረዋል።

ወጣቶች የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅና የህዝቧን ሰላም ለማረጋገጥ ህይወታቸውን ያለስስት ለመስጠት ያሳዩት ተነሳሽነት ክብርና አድናቆት እንደሚገባው ገልጸዋል።

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ በበኩላቸው፤ በመልካም ስነ ምግባር የታነጸ ቀና አስተሳሰብ ያለው ወጣት ለሀገር እድገትና ብልፅግና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ወጣቶች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በትግሥት በማለፍና በተሰማሩባቸው መስኮች ጠንክረው በመሥራት የኢትዮጵያን ከፍታ እንዲያረጋግጡ አሳስበዋል።

ወጣቶች ወደ ማህበረሰቡ በሚቀላቀሉበት ወቅት ባገኙትን እውቀት ከወገንተኝነት ርቀው ኢትዮጵያን ማገልገል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ወጣቶቹ የአገራቸውን አንድነት፣ አብሮነትንና ህብረ ብሄራዊነትን ለማጠናከር እንዲሰሩም መክረዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ለስልጠና የተገኙ ወጣቶች በሰጡት አስተያየት በአሸባሪው ህወሓት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት ለመደገፍ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያውያንን የአንድነት፣ የመከባበርና የመተሳሰብን እሴት ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም