ዳያስፖራ ምሁራን በአገራዊ ምክክርና ብሔራዊ መግባባት ግብዓት የሚሆን ዕውቀትና ተሞክሮ የሚያጋሩበት መድረክ ይመቻቻል

88

ታህሳስ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዳያስፖራ ምሁራን በአገራዊ ምክክርና ብሔራዊ መግባባት ግብዓት የሚሆኑ ዓለም አቀፍ ዕውቀትና ተሞክሮዎችን የሚያጋሩባቸው መድረኮች እንደሚመቻቹ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሣ ተናገሩ።

የሚኒስቴሩ እና የክልል ቢሮ የስራ ሃላፊዎች የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎችን አቀባበል አስመልክቶ "ለአገር ህልውና በአንድ ልቦና" በሚል መሪ ሃሳብ መግለጫ ሰጥተዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ በወቅቱ እንዳሉት ለአገራቸው ድጋፋቸውን ለማሳየት የሚመጡ ዳያስፖራዎችን ለመቀበል በአገር አቀፍ ደረጃ ተገቢው ዝግጅት ተከናውኗል።

ለእንግዶች አቀባበልም ኢትዮጵያን የሚገልጹ ባህላዊና ኪነ-ጥበባዊ ክዋኔዎች፣ ባዛርና ሲምፖዚየሞች፣ የባህልና ዘመናዊ ስፖርት ፌስቲቫሎች እና የዕደ-ጥበብ ውጤቶች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በሚዘጋጀው ሲምፖዚየምም ከውጭ የሚገቡ ምሁራን በአገራዊ ምክክርና ብሔራዊ መግባባት ግብዓት የሚሆኑ ዓለም አቀፍ ልምድና ተሞክሯቸውን የሚያጋሩበት ዕድል እንደሚፈጠር ገልጸዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ በበኩላቸው ለእንግዶቹ አቀባበል የተቋቋሙ ኮሚቴዎች ተግባራቸውን እየተወጡ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንግዶች በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች ያለስጋት እንዲንቀሳቀሱ በጸጥታ ረገድ አስተማማኝ ጥበቃ ለማድረግ ሃላፊነት መውሰዱን ገልጸዋል።

በእንግዶቹ አቀባበል የግሉ ዘርፍ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በተለይም ታዋቂ ግለሰቦች፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ስፖርተኞች እንግዶችን ለመቀበል ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የጠየቁት ደግሞ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲን ናቸው።

የአገርን ባህልና ገጽታ ግንባታን በማስተዋወቅ ረገድ ከሁሉም ክልሎች ከመጡ የዘርፉ ኃላፊዎች ጋር  እንደሚሰሩ ስምምነት ላይ መደረሱንም አመላክተዋል።

ክልሎቹን በመወከል የተናገሩት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሚስኪያ አብደላ፤ ክልሎች ከአገር ውጭ የሚመጡ እንግዶችን ተቀብለው ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

እንግዶችን ለመቀበል ከእያንዳንዱ ዜጋ ብዙ እንደሚጠበቅና የሁሉም አበርክቶ አስፈላጊ መሆኑ በመግለጫው ተጠቁሟል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም