የቁልቢ ቅዱስ ገብርዔል የንግሥ በዓል በሰላም ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የቁልቢ ቅዱስ ገብርዔል የንግሥ በዓል በሰላም ተጠናቀቀ

ሐረር፣ ታህሳስ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዓመታዊው የቁልቢ ቅዱስ ገብርዔል የንግሥ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም መጠናቀቁን በአካባቢው የተቋቋመው የጸጥታ ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።
በበዓሉም ምንም ዓይነት የስርቆት ወንጀልና የትራፊክ አደጋ አለመከሰቱም ተገልጿል።
የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢና የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ናስር መሐመድ እንዳሉት፤ በርካታ ምዕመናንና እንግዶች የታደሙበት በዓል ያለ ምንም የጸጥታ ችግር በሰላም ተጠናቋል።
በዓሉ ምንም ዓይነት የወንጀል ድርጊት ሳይፈጸም በሰላም ማብቃቱን አረጋግጠዋል።
በአካባቢው የጸጥታ ሥራ የተሰማሩት የምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ ዞኖች፣ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር፣ የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች በዓሉ በሰላም እንዲከበር አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም ምዕመንና በበዓሉ የታደሙ እንግዶች ወንጀልን በመከላከል ያላቸው ግንዘቤ በመጎልበቱና በመገናኛ ብዙሃን የተላለፉ መረጃዎች እገዛ ማድረጋቸውን ኮማንደር ናስር ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በበዓሉ ወቅት ያጋጥሙ የነበሩት የስርቆትና ሌሎች ወንጀሎች ዘንድሮ አለመከሰታቸውን አስታውቀዋል።
ምዕመናኑ ወደ በዓሉ ሥፍራ መምጣት ከጀመሩበት ከታህሳስ 17 ቀን 2014ዓም እስከ በዓሉ ዕለት ድረስ የትራፊክ አደጋ አለመድረሱንም እንዲሁ።
''በክብረ በዓሉ ሥፍራ ብቻ ሳይሆን ምዕመናኑ በየመንገዱም ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር ሳያጋጥማቸው በዓሉን እንዲያከብሩ የተሰራው የቅንጅት ሥራ ውጤታማ ሆኗል'' ያሉት ደግሞ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ የምስራቅ ኢትዮጵያ ፈጥኖ ደራሽ ዳይሬክተርና የኮማንድ ፖስቱ አባል ኮማንደር ሰለሞን ከበደ ናቸው።
ኮማንድ ፖስቱ በወንጀል መከላከል፣ በጥበቃ፣ በትራፊክና በሌሎችም ዘርፎች በቅንጅት ባከናወናቸው ሥራዎች በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከፍተኛውን ድርሻ ማበርከቱን ገልጸዋል።
ምዕመኑ ወደየመጡባቸው ሥፍራዎች እስኪመለሱም የሰላምና ጸጥታ ሥራዎች እንደሚቀጥሉም ኮማንደር ሰለሞን ጠቁመዋል።