ለአገር መከላከያ ሠራዊትና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ

158

ታህሳስ 19/2014/ኢዜአ/ በአዲስ አበባ የስራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስተባባሪነት ለአገር መከላከያ ሠራዊትና በጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ67 ነጥብ 3 ሚሊዮር ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ፡፡

በተደረገው ድጋፍ በአዲስ አበባ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች 23 ሚሊዮን ብር፤ የአዲስ አበባ ማህበራዊ ትረስት ፈንድ 20 ሚሊዮን ብር አበርክተዋል፡፡

ሠራተኛ አቅራቢ ማህበራት 12 ነጥብ 2 ሚሊዮን፣ አሰሪና ሠራተኛ ማኅበራት 11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር እና የስራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች 860 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የቀድሞ የቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ደግሞ የ500 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የአዲስ አበባ ማህበራዊ ትረስት ፈንድ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ደበበ ኤሮ በአገር ደረጃ የተጋረጡ ችግሮችን ለማቃለል በጋራ መስራት እንደሚገባ በመግለጽ ቦርዱ ከአገር የሚበልጥ ጉዳይ ባለመኖሩ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የስራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ተቋማቱ ድጋፉን ያደረጉት አገራቸውን በማስቀደም ካላቸው ላይ ቀንሰው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሴረኞች የአገራችንን ሠላም በማደፍረስ ኢኮኖሚያችንን ለመጉዳት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በተባበረ ክንድ ማክሸፍ አለብን ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አሸባሪው ህወሓት ወረራ ከጀመረባት ቅፅበት አንስቶ ሃብት በማሰባሰብ ለመከላከያ ሠራዊትና ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ላደረጉት ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡