በአማራ ክልል ከውጭ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል እየተደረገ ያለው ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው

220

ባህርዳር፣ ታህሳስ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ጥሪ ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል እየተደረገ ያለው ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ጣሂር ሙሀመድ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የገናና የጥምቀት በዓልን እንዲያሳልፉ በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ያሉ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድም በአዲስ አበባ፣ ደሴ፣ ላል ይበላ፣ ጎንደር እና ባህር ዳር በሚገኙ የቱሪዝም ጽህፈት ቤቶች ምዝገባ ተጀምሯል።

የኢትዮጵያዊያን መምጣት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት የተቀዛቀዘው የቱሪዝም ዘርፍ መልሶ እንዲነቃቃ በማድረግ በኩል ፋይዳ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ኃላፊው እንዳሉት፤ በክልሉ የሚገኙ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች በተለይ አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን አጥተዋል።

እንግዶቹን ለመቀበል በክልል ደረጃ አንድ አብይ ኮሚቴና በየደረጃው ንኡሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመው የዝግጅት ስራዎች  እየተጠናቀቁ መሆኑን አስረድተዋል።

እንግዶቹ እንዲጎበኟቸው ከተለዩት ቦታዎች መካከል ላል ይበላ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር እንዲሁም በአሸባሪው ቡድን ጉዳት የደረሰባቸው ቦታዎች ይገኙበታል።  

የተለያዩ የውይይት መድረኮች፣  አሸባሪው የፈጸመውን ግፍ እና  ቡድኑን በመታገል የተገኙ ገድሎችን  የሚያሳዩ አውደ ርዕይ እና  ሲምፖዚያም ለእንግዶቹ እንደሚዘጋጅም አቶ ጣሂር ተናግረዋል።

“አሸባሪው ህወሓት በለኮሰው ጦርነት የተፈጸሙ  ግፎች፣ የደረሰውን ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ወገኖቻችን በአካል ተገኝተው ሲመለከቱ በቀጣይ ለሚያደርጉት ትግል አጋዥ  ይሆናል” ብለዋል።

“የምንቀበለው በትግል ላይ የቆዩ ጀግኖችን ነው” ያሉት አቶ ጣሂር፤ የሚመጡ እንግዶችን በአግባቡ ለማስተናገድ ከሆቴል ማህበራትና ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

እንግዶቹ በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች የመብራት፣ የውሃ፣ የትራንስፖርት፣ የባንክና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማሟላት ከወዲሁ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼