በኢትዮጵያ 13 ሺህ ሄክታር የተራቆተ መሬት እንዲያገግም የሚረዳ መርሃ ግብር ይተገበራል

260

ታህሳስ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ 13 ሺህ ሄክታር የተራቆተ መሬት እንዲያገግም የሚረዳ መርሃ ግብር ይፋ ተደርጓል።

መርሃ ግብሩ በዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት፣ በኮሪያ ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ እና በግብርና ሚኒስቴር ትብብር የሚተገበር ነው።  

ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የደንና የመሬት ገጽታ ማገገሚያ በአማራ፣ በኦሮሚያና በሲዳማ ክልሎች የሚተገበረው መርሃ ግብሩ ከ9 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ይደረግበታል።

የኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ገመዶ ዳሌ እንደተናገሩት፤ መርሃ ግብሩ በሦስቱ ክልሎች የተመረጠ 13 ሺህ ሄክታር መሬትን ወደ ምርታማነት መመለስን ያካተተ ነው።  

‘ደን በራሱ አንድ የቢዝነስ ዘርፍ ነው’ ያሉት ዶክተር ገመዶ፤ ደንን በማልማት አነስተኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል እንዲጠቀም ማድረግ ሌላው የመርሃ ግብሩ አካል እንደሆነም አክለዋል።

ለዚህም በወረዳና ቀበሌ ያሉ ነዋሪዎች ደን ሲያለሙ የሚያስፈልጋቸው የእውቀት፣ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፎች የሚደረጉ ይሆናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሙቀት አማቂ ጋዞችን በመጠጥ ማስቀረት የሚያስችል የደን ልማት ስራው ምን ደረጃ ላይ እንዳለ መቃኘት በመርሃ ግብሩ የሚከናወን ሌላው ተግባር መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህም አገሪቷ የሚያስፈልጋትን የአቅም ግንባታ የሰው ኃይል ድጋፍ በማድረግ ውጤታማ ስራ እንዲከናወን ማገዝ የትኩረት ነጥቦች መሆናቸውን ገልጸዋል።

እንደ ዶክተር ገመዶ ገለጻ፤ በመርሃ ግብሩ አማራ፣ ኦሮሚያና ሲዳማ ክልሎች የታቀፉ ሲሆን ክልሎቹ በቅንጅት እንዲሰሩ የሚደረግ ይሆናል።

በኢትዮጵያ የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ሱንጉዋን ሺን በበኩላቸው ኤጀንሲው በኢትዮጵያ በጤና፣ በግብርና እና በሕዝብ አስተዳደር ላይ በትብብር ሲሰራ መቆየቱን አውስተዋል።

ኤጀንሲው የትብብር አድማሱን በማስፋት በአየር ንብረት ለውጥና አካባቢ ጥበቃ ላይ በጥምረት እየሰራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ‘ዛሬ ይፋ ያደረግነው መርሃ ግብርም የዚሁ አካል ነው’ ብለዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ተፈራ ታደሰ በበኩላቸው መንግሥት በደን ልማት ዘርፍ ውጤት ለማምጣት ስትራቴጂዎች ቀርጾ እየተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።

በአገሪቷ የሚከናወነው የደን ልማት ስራ ለኢኮኖሚው አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ሁሉን አቀፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ዓይነት ድጋፎች አይነተኛ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።