ዓይነስውሩ በአሸባሪው ህወሓት ለተጎዱ ወገኖች 60 ሺህ ብር ለገሱ

59

ሰመራ ታህሳስ 19/2014(ኢዜአ) ዓይነስውሩ አዛውንት በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ደጋፍ እንዲውል 60 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ ለገሱ።


ዕድሜያቸው 67 ዓመት እንደሆናቸው የሚናገሩት ሼህ አቡዱ አወል የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ ናቸው።

የሰባት ልጆች አባት የሆኑት ሼህ አቡዱ የወጣትነት ጊዜያቸውን በሾፌርነት አሳልፈዋል፤

ከ25 ዓመት በፊት በአንድ አጋጣሚ ድንገት በደረሰባቸው የተሽከርካሪ አደጋ ዓይነ ስውር እንደሆኑ ነው የሚገልጹት።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኑሯቸውን በቤተሰባቸው እገዛ እየመሩ መሆኑን የተናገሩት ሼህ አቡዱ፤ የሽብር ቡድኑን የጥፋት ሴራ በየጊዜው ሲከታተሉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

"በተለይም በአፋር እና በአማራ ክልሎች አሸባሪው ህወሓት በንጹሀን ዜጎች ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋና የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲሁም የመሰረተ-ልማት ውድመቶች በእጅጉ አሳዝኖኛል፤ እረፍትም ነስቶኛል" ይላሉ።

የዕድሜያቸው መግፋት በግንባር ጠላትን መፋለም ባያስችላቸውም የቤተሰባቸውን አባላት በማስተባበር በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች የሚችሉትን ገንዘብ አሰባስበው ነው ወደ አፋር የመጡት።

ያሰባሰቡትን 60 ሺህ ብር ጥሬ ገንዘብ በአፋር ክልል በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ለተጎዱ ወገኖች እንዲውል ዛሬ ለክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ አስረክበዋል።

"ይሄን ያህል ኪሎ ሜትር ርቀት አቋርጨ የመጣሁት ድጋፍ ይዤ መጣሁ ለማለት ሳይሆን የጀግንነት ታሪክ የሰራውን የአፋር ህዝብ ወገኔን ለማየትና መሬቱን ረግጬ ለመመለስ ጭምር ነው" ብለዋል ሼህ አቡዱ ።

የህወሓትን የጥፋት ተልዕኮ ለማክሸፍ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ በጀግንነት ተዋድቆ ታሪክ ለሰራው የአፋር ህዝብ ያላቸውን አክብሮትና ወገናዊ አጋርነት በአካል ተገኝተው ለመግለጽ በመቻላቸውም ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ነው የገለጹት።

ድጋፉን የተረከቡት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ፤ የሼህ አቡዱን በጎ ተግባር በማሞገስ አሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር ከልሎች ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ሀብት ማውደሙን አውስተዋል።

የሽብር ቡድኑ ከአቅመ ደካማ እስከ አካል ጉዳተኛ ድረስ ለዓመታት ያፈሩትን ጥሪት ከመዝረፍና ከማውደም ባለፈ ከሰብአዊነት የወጣ የጭካኔ ተግባር መፈጸሙንም አመልክተዋል።

የአሸባሪው ህወሓት ዓላማ ኢትዮጵያን በማፍረስ ዜጎቿን ለሰቆቃ መዳረግ መሆኑን የተገነዘቡት ኢትዮጵያውያን ጠላትን በጋራ ከመመከት ጀምሮ ተጎጂዎችን ለመደገፍ እየተረባረቡ መሆኑንም ተናግረዋል።

"በተለይም የሼህ አብዱ ድጋፍ ሰው ሲተርፈው ብቻም ሳይሆን ፍላጎቱን ገትቶና ካለው ቀንሶ ለወገኖቹ አለሁ ማለትን በሚገባ የሚያስተምር ትልቅ አርአያነት ያለው ተግባር ነው" ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

ከወልቂጤ መጥተው ለአፋር ወገኖቻቸው ያላቸውን ክብርና ፍቅር ለመግለጽ ባደረጉት ጥረት በክልሉ መንግስትና ህዝብ ስም አቶ አወል ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም