ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በአሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ 67 ሰዎች በግፍ ሲገደሉ 12 ሴቶች ደግሞ አስገድዶ የመድፈር ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል

114

ታህሳስ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ 67 ሠላማዊ ሰዎችን በግፍ መጨፍጨፋቸውንና 12 ሴቶችን የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንደተፈጸመባቸው የዞኑ አስተዳዳር ገለጸ፡፡

በዞኑ አሸባሪው ህወሓት ወረራ በፈጸመበት ወቅት 6 ሆስፒታሎችና ከ180 በላይ ትምህርት ቤቶችን አውድሟል፤ ዘርፏል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረጻድቅ በሰጡት መግለጫ አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ተቀናጅተው በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ንጹሃንን በግፍ መጨፍጨፋቸውን አመልክተዋል።

በዚህ የግፍ ድርጊት 67 ንጹሐን ሲገደሉ 12 ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሰለባ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የህወሓት ወራሪ ንጹሃንን ከመጨፍጨፋም ባለፈ የጤና፣ የትምህርትና መሰል ተቋማትና መሰረተ ልማቶችንም አውድሟል ብለዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ሕዝብ ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጋር በመተባበር አሸባሪዎቹን ከአካባቢው ማስወጣቱን ገልጸው፤ በጥቃቱ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን የማቋቋም ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ በሰሜን ሸዋ ዞን አምስት ወረዳዎች ላይ ከፍተውት በነበረው ጥቃት የበርካቶችን ህይወት መቅጠፋቸውን አስታውሰዋል።

የተጎጂ ቤተሰቦችንና የተፈናቀሉትን ለማቋቋም በሚደረገው እንቅስቃሴ መላው ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ርብርብ እንዲያደርጉ አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም