በሽብር ቡድኑ ለተጎዱ አካባቢዎች ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል በላይ የምግብ እህል ሊቀርብ ነው

56

ባህርዳር ታህሳስ 19/2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የምግብ እህል ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ኮሚሽን አስታወቀ ።


የኮሚሽኑ የግብይት ዳይሬክተር አቶ ዓለምዘውድ ስሜነህ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሃት ወረራ በፈጸመባቸው ሰባት ዞኖች በመኸር ምርት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

አሸባሪው በአማራ ክልል ወረራ የጀመረው በዘር ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩን ከምርት ውጭ ማድረጉን ጠቁመው፤ በዘር የተሸፈነውም ውድመት ስለደረሰበት የሚጠበቀውን ያህል ምርት አለመገኘቱን ተናግረዋል።

ችግሩን ለማቃለል ዩኒየኖችንና የህብረት ስራ ማህበራትን በማስተባበር ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የምግብ እህል ምርት ካለባቸው የክልሉ አካባቢዎች በመግዛት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በወረራው ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎችም ከሚቀርቡ መካከልም ጤፍ፣ በቆሎ፣ ስንዴና አተር እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ምርቱን ለተጠቃሚው በቀጥታ ለማድረስም በአካባቢው ከሚገኙ ዩኒየኖችና ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ጋር ትስስር በመፍጠር እንደሚሰራም አቶ ዓለም ዘውድ አስረድተዋል።

በሌላ በኩል 196 ሺህ ኩንታል የሰሊጥ፣ የቦሎቄና ሌሎች ምርቶችን ከአምራቹ በመግዛት ለወጭ ንግድ በማዋል የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስትም የህብረት ስራ ማህበራት ከ896 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር በዋስትና እንዲያገኙ በዓባይና በኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በኩል ማመቻቸቱን አስታውቀዋል።

በእንጂባራ ከተማ የሚገኘው የአድማስ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ መሰረት ወርቄ በበኩላቸው፤ በወረራ ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች ከ183 ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እህል በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ግዥ እየተፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል።

ምርቱን ለማቅረብም ከአቻ ዩኒየኖችና የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ባሻገር ከክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ጋር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት ለዩኒየኖች የግብይት ማከናወኛ በዋስትና ብድር ማመቻቸቱ ለወገን ለመድረስ የያዙትን ግብ ለማሳካት እንደሚያግዛቸውም ጠቅሰዋል።

ባለፉት አምስት ወራትም በዩኒኖችና ህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት 26 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የተለያየ የሰብል ምርትና የዳቦ ዱቄት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ማቅረብ መቻሉን ኮሚሽኑ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም