ሀገሪቱ የገጠማት ተግዳሮት ፈታኝ ቢሆንም ታግሎ በማለፍ ዳግም የአፍሪካዊያን ኩራት የምትሆንበትን እድል ይፈጥራል

83

ሀዋሳ ፤ታህሳስ 19/2014 (ኢዜአ ሀገሪቱ የገጠማት ተግዳሮት ፈታኝ ቢሆንም በፅናት ታግሎ በማለፍ ዳግም የአፍሪካዊያን ኩራት የምትሆንበትን እድል ይፋጥራል ሲሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከተለያዩ የውጭ ሀገራት በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት ለመጡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ትናንት ምሽት በሀዋሳ ኃይሌ ሪዞርት የእራት ግብዣ አድርገዋል።

በዚህ ወቅት እንዳሉት፤  የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ለሀገራቸው ክብርና አንድነት ሲሉ በየግንባሩ ተዋድቀዋል።

ሆኖም ከፋፋይና ኢትዮጵያ ጠል በሆነው በአሸባሪው የህወሓት ሥርዓት ተገፍተው ከሚወዷት እናት ሀገራቸው ለመውጣት መገደዳቸውን   አስታውስዋል።

ይሁንና ዛሬም ሀገሪቱ የህልውና አደጋ በተጋረጠባት ወቅት  ለእናት ሀገራችን  እስከ ሕይወት መስዋዕትነት እንክፍላለን ብለው ወደ ሀገር ቤት በመምጣት ዳግም የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናቸውን አስመስክረዋል ብለዋል።

ዛሬ በአጋጣሚ ህዝብ የማስተዳደር ኃላፊነት ላይ ብንሆንም ለሀገር ክብርና ነፃነት እስከምን ድረስ መስዋዕትነት መክፈል እንደሚገባን ከእናንተ እንማራለን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።

ኢትዮጵያውያን ጥንትም የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ቀንዲል ነን ያሉት አቶ ርስቱ ፤ አሁን የገጠመን የህልውና አደጋ ምንም እንኳ ፈታኝ ቢሆንም በፅናት ታግሎ በማለፍ ዳግም የአፍሪካዊያን ኩራት መሆን የሚቻልበት እድል እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።

ከመኮንኖቹ መካከል የቀድሞ የአየር ኃይል አባል  ኮሎኔል ክንፉ ሀብተወልድ በበኩላቸው፤ በተደረገላቸው ግብዣና መስተንግዶ መደሰታቸውን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ፈተና በገጠማት ወቅት በተለይ በተስፋፊው የዚያድባሬ መንግስት ወረራን ለማክሸፍ በጦርነቱ መሳተፋቸውን አሰታውሰዋል።

በዚህ ገድል ውሰጥ ከደቡብ ኢትዮጵያ ሠራዊቱን የተቀላቀሉ በርካቶች በጀግንነትና በቆራጥነት መዋደቃቸውንና የሕይወታት መስዋእትነት መክፈላቸው አውስተዋል ።

አሸባሪው ህወሓትና ጋላቢዎቹ በሚነዙት የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ፣ ተሸንፋለች የሚል  ውዥንብር ከሀገር ውጭ ሆኖ መስማት እጅግ የሚያም እንደሆነ ጠቅሰው፤ ለእናት ሀገራችን የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ኢትዮጵያ ወይም ሞት በማለት መጥተናል ነው ያሉት።

ወደ ሀገር ከመጡ በኋላ በመላ ሀገሪቱ የተመለከቷት ኢትዮጵያ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራትና ሚዲያዎቻቸው ከሚነዙት በእጅጉ የተለየና ፍጹም ሠላማዊ ድባብ እንዳለ ማረጋገጥ እንደቻሉ ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት ለመኮንኖቹ የደቡብ ክልል ብሔር ብሔረሰቦችን የሚገልፁ የተለያዩ የባህል አልባሳት በስጦታ አበርክቶላቸዋል።

በመርሀ-ግብሩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎ እና ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች ተገኝተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም