ቆቦ ወደ ቀድሞ ሠላማዊ እንቅስቃሴዋ እየተመለሰች ነው

103

ታህሳስ 19 / 2014(ኢዜአ) ከአሸባሪው የህወሓት ወራሪ ኃይል ነጻ የወጣችው የቆቦ ከተማ ወደ ቀድሞ ሠላማዊ እንቅስቃሴዋ እየተመለሰች መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ።

የሽብር ቡድኑ በአማራና በአፋር ክልል አካባቢዎች በቆየባቸው ጊዜያት በዜጎች ላይ ሠብዓዊ፣ማኅበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳቶችን አድርሷል።

የቆቦ ከተማም የተጠቀሱት ጉዳቶች ከደረሱባቸው አካባቢዎች መካከል ትጠቀሳለች።

እንደ ከተማዋ ነዋሪዎች ገለጻ፤ የሽብር ቡድኑ በዚያ በቆየባቸው ጊዜያት የሴት ልጅን ኪስ ጭምር በመፈተሽ ገንዘብ እስከመቀማት የደረሰ ወንጀል ፈጽሟል።

በቤተ-እምነቶች የኃይማኖት አባቶችን በማስገደድ "በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላችሁን ተሰሚነት ተጠቅማችሁ ጥሩ ሰው ናቸው ብላችሁ መስክሩ" እያሉ ከፍተኛ ማንገላታትና ጫና ሲያደርጉም ነበር።

May be an image of 2 people and road

የሽብር ቡድኑ ወራሪዎች የኃይማኖት ተቋማት ንብረቶችን በማስወጣት ቤተ-እምነቶችን የከባድ መሳሪያ ምሽግ አድርገው መጠቀማቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

የወገን ጦር በሽብር ቡድኑ ወራሪ ላይ ድል ከተቀዳጀ በኋላ ከተማዋ ወደ ቀድሞ ሠላማዊ የሥራ እንቅስቃሴ እየተመለሰች ነው ሲሉም ገልጸዋል ነዋሪዎቹ።

አርሶ አደሩ የእርሻና የመኸር ሥራውን፤ ከተሜውም የንግድ ሥራውን እየከወኑ ነው ብለዋል።

ነዋሪዎቹ የሽብር ቡድኑ በከተማዋ የመንግስትና የግል ድርጅቶች ላይ ጭምር ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት ማድረሱን፤ በርካታ ዜጎችም ለሠብዓዊ ቀውስ መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

ያለው ለሌለው እያካፈለ የቆየ ቢሆንም አሁን መንግስት፣ግብረሰናይ ድርጅቶችና በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመለየት የጤና እና የሠብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎትን ጨምሮ ሱቆች ምግብ ቤቶችና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫዎች ስራ እየጀመሩ መሆኑን ኢዜአ ባደረገው ምልከታ መታዘብ ችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም