ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ8 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

207

ደሴ/ደብረ ብርሀን ፤ ታህሳስ 18/2014(ኢዜአ) በአሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ የጥፋት ድርጊት በአማራና አፋር ክልሎ ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ8 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የምግብ እህልና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።

ድጋፉን ያደረጉት የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በደሴ ከተማ፤ ኢትዮ ኢንጂነርንግ ግሩፕ ደግሞ በደብረ ብርሀን ከተማ ነው።

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌታሁን ነጋሽ በወቅቱ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳው አሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር ህዝብ ላይ የፈፀመው ግፍና መከራ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ልብ ሰብሯል፤ አሳዝኗል፡፡

“አሸባሪው ቡድን በታሪክ የሚመዘገብ አሳፋሪ ድርጊት ቢፈፅምም ኢትዮጵያውያን ከቅድመ አያቶቻቸው ያገኙትን የመተጋገዝ፤ የመረዳዳትና የአብሮነት ባህልና እሴት ተጠቅመው ሁሉንም ችግር በድል ያልፉታል፤ እያለፉትም ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡

ድርጅቱ የወደመውን ንብረት መልሶ ለማቋቋምና ተጎጂዎችን ለመደገፍ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ኃላፊነቱን ለመወጣት ቆርጦ መነሳቱንም ነው ያስታወቁት።

ድርጅቱ ዘንድሮ የተመሰረተበትን 100ኛ ዓመት ለማክበር አቅዶ እንደነበረ ጠቁመው፤ አመራሩ፣ ሠራተኛውና የሙያ ማህበሩ የተጎዱ ወገኖች እየተቸገሩ ለድግስና ለደስታ የምናወጣው ወጭ የለም፣ በጀቱም ለተፈናቃዮች ይሁንልን በሚል ውሳኔ ማሳለፋቸውን አስረድተዋል፡፡


አጋር አካላትን በማስተባበር ጭምር ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ በሚገመት ወጭ በማድረግ በአማራና አፋር ለተፈናቀሉ ዜጎች ዛሬ ድጋፍ አድርገዋል፡፡


በዚህም በደቡብ ወሎና አካባቢው ለሚገኙ ወገኖች እንዲውል 2 ሚሊዮን ብር ግምት ያልው 360 ኩንታል ዱቄት፣ 210 ካርቶን ዘይት፣ 100 ካርቶን አልሚ ምግብ፣ 64 ካርቶን የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስና 30 ኬሻ አልባሳት በደሴ ከተማ አስረክበዋል።


ቀሪው 4 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ተመሳሳይ ዓይነት ድጋፍ ወደ ደብረ ታቦርና ሰመራ ከተሞች መላኩን አስታውቀዋል።


የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሳይ ማሩ በበኩላቸው ብርሃንና ሰላም ድርጅት ዛሬ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፣ ሁሉም በሚችለው የተጎዱትን እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡


በተመሳሳይ ኢትዮ ኢንጂነርንግ ግሩፕ በአሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ ለተፈናቀሉ ወገኖች 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።


የግሩፑ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሞላልኝ ካሳቴ ብርሃን በደብረ ብርሀን ከተማ ተገኝተው ድጋፉን ሲያስረክቡ እንዳሉት፤ በአሸባሪው ህወሓት እና ሸኔ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በመነሳት የሀገር ክህደት ፈፅመዋል።


በዚህም ዜጎች ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው ለከፋ ችግር በመጋለጣቸው አምራችና ለጋስ የነበረው እጃቸው ለድጋፍ በመዘርጋቱ ማዘናቸውን ተናግረዋል።

የዜጎችን ችግር ለማጋራትም የግሩፑ ሰራተኞች ቀደም ሲል የወር ደመወዛቸውን መስጠታቸውን አስታውሰው፤ አሁንም ከኪስ ገንዘባቸው በማዋጣት 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረፃድቅ በበኩላቸው፤ የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ሰራተኞች ያደረጉት ድጋፍ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች በፍትሃዊነት እንደሚሰራጭ አረጋግጠዋል።

በተለይም በውጭ የሚኖረው ዳያስፖራ በአካባቢው ባለው የኢንቨስትመንት አማራጭ በመሳተፍ የህዝቡን እምባ በስራ እድል ፈጠራ እንዲያብስም ዋና አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል።