በካማሽ ዞን የእርስ በእርስ ግጭትና በ27 ሰዎች ሞት የተከሰሱ ዘጠኝ ግለሰቦች እስከ 21 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ተቀጡ

277

አሶሳ፤ ታህሳስ 18 / 2014 (ኢዜአ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አሶሳ እና አካባቢው አንደኛ ተዘዋዋሪ ችሎት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን በ27 ሰዎች ሞት ክስ ከተመሰረተባቸው 48 ሰዎች መካከል በዘጠኙ ላይ ከ8 እስከ 21 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑ ተገልጿል፡፡

ከሳሹ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጸው፤ ከመስከረም 17 እስከ ህዳር ወር መጨረሻ 2011 ዓ.ም በክልሉ ካማሽ ዞን “አጋሎሜጢ ወረዳ” እና አጎራባች አሮሚያ ክልል አካባቢዎች ተከስቶ በነበረ ግጭት የ27 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡


በግጭቱ በርካታ ሰዎች የአካል ጎዳት ሲደርስባቸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችም ከቀያቸው ተፈናቅለው ነበር።


በእነገመቹ ጉተማ የክስ መዝገብ በተዘረዘሩ 15 ክሶች የእርስ በርስ ግጭት በማስነሳት እና በመሳተፍ እንዲሁም በከባድ የግድያ ወንጀል በ48 ሰዎች ላይ ክስ ተመስርቶ ጉዳዩ ሲታይ ቆይቷል።


በዚህም የቀረበባቸውን የወንጀል ክስ መከላከል ያልቻሉ ዘጠኝ ተከሳሾች ላይ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አሶሳ እና አካባቢው አንደኛ ተዘዋዋሪ ችሎት ታህሳስ 15 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ጉዳያቸውን በመመልከት የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።


ፍርድ ቤቱ በአሶሳ ከተማ በዋለው ችሎት ተከሳሾቹ ከስምንት እስከ 21 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል።


በዚህም መሠረት 40ኛ ተከሳሽ ተሊንቲ ሙለታ ኩምሳ፣ 41ኛ ተከሳሽ በሊና ቦረና ሃጂን እና 42ኛ ተከሳሽ ሰንበታ ጉደታ ዲቢሳ እያንዳንዳቸው በ21 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጥተዋል።


በሌላ በኩል 18ኛ ተከሳሽ ታፈሰ መርጋ ጢሎ፣ 24ኛ ተከሳሽ ንብረት ገለታ ቤዶ፣ 32ኛ ተከሳሽ ጸጋ ታዬ ሲዳ፣ 36ኛ ተከሳሽ አመንቴ እሬሳ ከሚሰ እና 44ኛ ተከሳሽ ዳንኤል ቡሽራ ኩሜ እያንዳንዳቸው በዘጠኝ ዓመት እንዲሁም 39ኛ ተከሳሽ አድማሱ ፋራ ዋልተጂ በስምንት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑ ተመልክቷል።


በፖሊስ ተፈልገው ያልተገኙ ቀሪ ተከሳሾች የክስ መዝገብ ለጊዜው ተቋርጦ ተፈልገው በሚቀርቡበት ወቅት ጉዳያቸው እንደገና እንዲታይ ተዘዋዋሪ ችሎቱ መወሰኑን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ አስታውቋል፡፡