የኢትዮጵያውያን የበቃ ንቅናቄ የምዕራባውያንን ጭምብል ሲያስወልቅ አፍሪካውያንን አንቅቷቸዋል

234

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18/2014 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያውያን የበቃ ንቅናቄ የምዕራባውያንን ጭምብል ሲያስወልቅ አፍሪካውያንን ደግሞ አንቅቷቸዋል ሲሉ ሶማሊያዊው ከፍተኛ ዲፕሎማት ሻፊቅ ዩሱፍ ኦማር ተናገሩ።

ኢትዮጵያዊያን እና ትልውደ ኢትዮጵያውያን በሀገራችን ጉዳይ አንደራደርም ብለው የበቃ እንቅስቃሴን ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

የምዕራባውያንን በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ሙከራ በመቃወም የአሜሪካና የአውሮፓ ከተሞችን በሰልፍ አጥለቅልቀዋል።


ይህ የኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አንድነት ከአደባባይ ሰልፍ እስከ ዲጂታሉ ዓለም የተዘረጋ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሌሎች አፍሪካውያን እና በዓለም ዙሪያ ያሉ ጥቁር ህዝቦች ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ አድርጓል።

በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ዲፕሎማቱ ፕሮፌሰር ሻፊቅ ዩሱፍ ኦማር ኢትዮጵያ እየከፈለችው ያለው ዋጋ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ አንድነት የተከፈለ ዋጋ ነው ብለዋል።

የበቃ ንቅናቄን የጀመሩት ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች በተለይም ጋዜጠኞች እና የህግ ባለሙያዎች መሆናቸውን የገለፁት ፕሮፌሰር ሻፊቅ፥ ንቅናቄው አፍሪካውያንን ከእንቅልፋቸው ቀስቅሷል ነው ያሉት።

የበቃ ዘመቻው በውጭ ሀገራትና በሀገር ውስጥ ተጠናክሮ በመቀጠሉ የምዕራባውያንን ጭምብል አስወልቋል ሲሉም ተናግረዋል።

እንደ ዲፕሎማቱ ገለፃ አንዳንድ የምዕራባውያን ፖለቲከኞች አሁን አፍሪካን ዳግም ቅኝ የምንገዛበት ወቅት ላይ በመሆናችን ጠንካራዋን እና የአፍሪካ እናት የሆነችውን ኢትዮጵያን እናፈራርሳት ብለው ተነስተዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው ጦርነት በመላው አፍሪካውያን ላይ የተከፈተ በመሆኑ እኔም ሆንኩ ሌሎች አፍሪካውያን ቤተሰቦቻችንን፣ ሀገራችንን እና አፍሪካን ለመታደግ ከኢትዮጵያ ጎን መቆም አለብን ብለዋል።