መንግስት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ለመወሰን በተሻሻለው ረቂቅ መመሪያ ላይ ውይይት ተካሄደ

151

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18/2014 ( ኢዜአ) መንግስት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ለመወሰን በተሻሻለው ረቂቅ መመሪያ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወያይተዋል።

ውይይቱ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመቻችነት ነው የተካሄደው።

የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የተሻሻለው ረቂቅ መመሪያ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያደርጉትን ትግል ለማጠናከር ይረዳል ብለዋል።

ለመመሪያው መሻሻል መነሻ የሆነው መንግስት የሚሰጠው ድጋፍ መስፈርት፣ ቀመርና አጠቃቀም ግልጽ በሆነ መልኩ ለመከወን መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዘለቄታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ያስችላል ነው ያሉት።

በተሻሻለው ረቂቅ መመሪያ መሰረትም ፓርቲዎች ድጋፉን ለዜጎች የፖለቲካ እውቀት ማሳደጊያ፣ ተሳትፎ ማጠናከሪያ፣ ፓርቲውን ለማስተዋወቅ፣ የምረጡኝ ቅስቀሳ ለማድረግና ሴቶችና አካል ጉዳተኞችን ለማካተት ጥቅም ላይ እንዲያውሉት ይገደዳሉ ብለዋል።

የድጋፍ አሰጣጥ መስፈርቱም ፓርቲዎች ካሏቸው የአባላት ብዛትና ከእነሱም በሚያገኙት ገቢ፣ በሴት ዕጩዎችና አባላት ብዛት እንዲሁም በምርጫ ባገኙት የመራጮች ድምጽ መጠን እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም አጠቃላይ ምርጫ በሚደረግበት ዓመት ድጋፉ በምርጫ ለሚሳተፉ ሁሉም ፓርቲዎች 25 በመቶ ይከፋፈላል ብለዋል።

ፓርቲዎች በሚያቀርቡት የዕጩ ብዛት መሰረት 25 በመቶ፤ ለውድድር በሚያቀርቧቸው ሴት ዕጩዎች ብዛት ደግሞ 20 በመቶ ድጋፍ ያገኛሉ።

ባሏቸው የሴት አመራሮች ብዛት 15 በመቶ እንዲሁም የአካል ጉዳተኛ ዕጩዎች ብዛት ደግሞ 10 በመቶ ድጋፍ የሚያገኙ ይሆናል።

ምርጫ በማይደረግበት ዓመት ወይም በመደበኛ ጊዜ 35 በመቶ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በአባላት ብዛት፣ በሴት አባላት ብዛትና በሴት አመራር ብዛት መሰረት 15 በመቶ ይደርሳቸዋልም ብለዋል።

ቦርዱ በሚያዘጋጀው አሰራር መሰረት ድጋፉን የማከፋፈል፣ ክፍፍሉ የሚደረግበትን መስፈርትና ቀመር ተግባራዊ ያደርጋል ብለዋል ሰብሳቢዋ።

እንደ ሰብሳቢዋ አገላለጽ ድጋፉን ለተገቢው ዓላማ በማያውሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የተጠያቂነትና የቅጣት እርምጃም ይወሰዳል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው፤ በተሻሻለው ረቂቅ መመሪያ ላይ መካተትና መቀነስ አለባቸው ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ሐሳብ ሰጥተዋል።

መመሪያው አዳዲስ የፖለቲካ ድርጅቶችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲሻሻል እንዲሁም በአባላት ብዛት መሰረት የሚሰራው ቀመርም በአግባቡ ቢጤን ብለዋል።

ከዚህም አልፎ ከአባላት የሚሰበሰበውን መዋጮ ታሳቢ አድርጎ የሚሰራው ቀመር በድጋሚ ቢታይ ሲሉም አንስተዋል።

ቀመሩ በቀደመው ምርጫ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በሚያበረታታ መልኩ ቢሆን ፓርቲዎች እንዳይፈርሱ የሚያግዝ በመሆኑ ከፍ ያለ ዋጋ ቢሰጠው ሲሉም አመልክተዋል።

በፖለቲካ ፓርቲዎቹ የተነሱ ሐሳቦች ለግብዓትነት የሚጠቅሙና መሻሻል ያለባቸው ሐሳቦችም የሚካተቱ መሆኑን የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ ከአባላት መታሰርና መንገላታት ጋር በተያያዘ በተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፤ ማጣራት እንደሚደረግ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም