አሸባሪው የህወሓት ቡድን የጥራሬ ወንዝ ላይ የተገነቡ ሁለት ትላልቅ ድልድዮችን አውድሟል

309

ባህር ዳር ፤ ታህሳስ 18/2014(ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በሚገኘው የጥራሬ ወንዝ ላይ የተገነቡ ሁለት ትላልቅ ድልድዮችን ማውደሙን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪ አስታወቁ።

ምክትል አስተዳዳሪው አቶ ተስፋዬ ገብሬ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አሸባሪው  ቡድን ድልድዮቹን ያወደማቸው በአካባቢው ወረራ በፈጸመበት ወቅት ነው።

በዚህም ከሰቆጣ-ኮረም-አዲስ አበባ የሚያገናኘውን የብረት ድልድይ እና ከሰቆጣ ወደ ፃግብጅ ወረዳ የሚያሸጋግረው ከፍተኛ የኮንክሪት ድልድይ ከጥቅም ውጭ መሆናቸውን ተናግረዋል።

“ይህም የዋግ ብሔረሰብ ከሌሎች የሀገሪቱ ህዝብ ጋር እንዳይገናኝ ፀረ ህዝብ ባህሪውን በተግባር ያሳያል” ብለዋል።

ከዚህም ሌላ የሽብር ቡድኑ  የጤና፣ የትምህርት ተቋማትና የግለሰብ ንብረት እንዲሁም የመንግስት ቢሮዎችን ሲዘርፍ ያልቻለውንም ማጥፋቱን ጠቅሰዋል።

ቡድኑ በስልጣን በቆየባቸው ዘመናት የዋግ ህዝብ የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ሲሰራ መቆየቱን ያስታወሱት ምክትል አስተዳዳሪው፤ “አሁንም የተሰሩ መሰረተ ልማቶችን በማውደም ህዝብን በማጎሳቆል ያዳበረውን ባህሪ በተጨባጭ አሳይቷል” ብለዋል።

በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከአሸባሪው ህወሓት ነፃ በወጡ ከተሞች የንግድ እንቅስቃሴዎችና የመንግስት ተቋማትን አገልግሎት ለማስጀመር እየሰራ መሆኑንም አቶ ተስፋዬ  ጨምረው ገልጸዋል።