ወደ አገር ቤት ለሚመጡ የዳያስፖራ አባላት የተዘጋጁ ሁነቶች ይፋ ሆኑ

235

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18/2014 ( ኢዜአ)  የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ለመቀበል ሲደረግ የነበረው ዝግጅት ተጠናቋል።

ለዳያስፖራው የተዘጋጁ መርሃ ግብሮችም ይፋ ተደርገዋል።


ወደ ሀገር ቤት ለሚመጡ የዳያስፖራ አባላት የሚደረገውን አቀባበልና የሚካሄዱ መርሃ ግብሮችን እንዲያስተባብር የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ የአቀባበል ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልጿል።

የዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኮሚቴው ሴክሬታሪያት ዶክተር መሐመድ እንድሪስ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ ሀገራቸው ሲመጡ የተዘጋጁ መርሃ ግብሮች የሚካሄዱበትን የጊዜ ሰሌዳ ይፋ አድርገዋል።

በዚህም መሰረት ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም አጠቃላይ የመክፈቻ መርሃ ግብር በወዳጅነት አደባባይ ይካሄዳል።

ታህሳስ 24 ቀን በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ጉብኝት፣ ታህሳስ 26 ቀን ደግሞ በመዲናዋ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መዘጋጀቱን ነው የገለጹት።

ዳያስፖራው ለመልሶ ግንባታና ማቋቋም ተግባር አስተዋጽኦ እንዲያደርግ በተለያዩ አካባቢዎች በአካል ጉብኝት የሚያደርግበትን መርሃ ግብርም ዘርዝረዋል።

ዳያስፖራው በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን ሚና በተመለከተ የምክክር መድረኮች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ታህሳስ 28 እና 29 ገናን በላሊበላ ከተማ የማክበር ስነስርዓት የሚካሄድ ሲሆን፣ የደም ልገሳ፣ የአደባባይ ምስጋና እንዲሁም ለመከላከያ ሰራዊት ቤተሰቦች የበዓል ስጦታ መርሃ ግብርና ሌሎች ሰፊ ሁነቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

የኮሚቴው አባል የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ዣንጥራር ዓባይ ከተማዋ ዳያስፖራውን ለመቀበል እንደ ሀገር ከተዘጋጀው መርሃ ግብር ጋር በመቀናጀት ከጸጥታ ጀምሮ ዝግጅቷን ማጠናቀቋን ጠቅሰዋል።

የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው ዳያስፖራው የሀገሩን ገጽታ የሚያሳይባቸው የቱሪዝም ጥቅል አገልግሎቶች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ኦፕሬሽናል ስራውን በንዑስ ኮሚቴነት የሚያስተባብሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ዳያስፖራው ሀገራዊ ጥሪውን ተቀብሎ ለመምጣት እያሳየ ያለው ተነሳሽነት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው የአቀባበል ዝግጅቱ ተጠናቋል ብለዋል።

ዳያስፖራው በዚህ ወቅት ወደ ሀገሩ መምጣቱ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ተናግረዋል።

የተዘጋጁ ትላልቅ መርሃ ግብሮች እስከ ጥር 15 ቀን 2014 ዓ.ም የሚቀጥሉ ሲሆን ዳያስፖራው በተመቸው ጊዜ ወደ ሀገር ቤት እንዲመጣ ጥሪው ዓመቱን ሙሉ ይቀጥላል ተብሏል።