የጉራጌ ማህበረሰብ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዝ አማካሪ ምክር ቤት ተቋቋመ

83
አዲስ አበባ ነሃሴ 20/2010 የጉራጌ ማህበረሰብ የልማትና ተጠቃሚነት ችግሮች የሚፈቱበትን መላ የሚዘይድ አማካሪ ምክር ቤት ተቋቋመ። ምክር ቤቱ የተቋቋመው በጉራጌ ልማት ማህበር አማካኝነት ነው። የማህበሩ አባላት በጉራጌ ማህበረሰብ ውስጥ ጎልተው በሚታዩ ችግሮችና የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ ዛሬ ተወያይተዋል። በዚህ ወቅት በጉራጌ ህዝብ ዘንድ የሚታዩ የፖለቲካ፣ የልማትና ተጠቃሚነት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አደረጃጀት እንዲያዘጋጅ ቀደም ሲል በማህበሩ የተቋቋመው ጊዜያዊ ኮሚቴ ያቀረበው ምክረ-ሀሳብ ለአባላቱ ቀርቧል። የኮሚቴው ጸኃፊ አቶ ክፍሌ ሰብካዝ እንደገለጹት በጉራጌ ዞን ተገቢነት ያለው አስተዳደራዊ መዋቅር አለመኖር፣ ብሄረሰቡ በሚታወቅበት የንግድ ሥራ ውስጥ ያለው ስርዓት ፍትሃዊ አለመሆንና ተገቢ የፖለቲካ ውክልና አለማግኘት የጉራጌ ማህበረሰብ ካሉበት ማነቆዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው። "በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው አንድነት ደካማ መሆንና በአካባቢው ተወላጅ ምሁራን በኩል ያለው ተሳትፎም በአግባቡ የተደራጀ አለመሆን ለማህበረሰቡ ችግሮች ምክንያት ተደርገው የሚወሰዱ ክፍተቶች ናቸው" ብለዋል። ከዚህም ሌላ "በገጠሩ ክፍል የሚኖረው የጉራጌ ማህበረሰብ የሥራ ባህል እየተዳከመ መምጣቱ" ሌላው በአካባቢው እየታየ ያለ ችግር ነው ተብሏል። በመሆኑም እነዚህና ሌሎች የማህበረሰቡን የልማትና የተጠቃሚነት ተግዳሮቶች መፍታት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ አማካሪ ምክር ቤት ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ኮሚቴው በምክረ-ሀሳቡ ላይ ጠቁሟል። የማህበረሰቡን የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማህበራዊና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች የሚፈቱባቸውን ስልቶች መቀየስ የአማካሪ ምክር ቤቱ ዋነኛ ተግባር ይሆናል ተብሏል። በምክር ቤቱ ስር የንግድና ኢንቨስትመንት፣ የወጣቶች ድጋፍና ክትትል፣ የልማትና ባህል፣ የአንድነትና ወዳጅነት እንዲሁም የአደጋ መከላከልና አቅርቦት ንዑስ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ሥራቸውን እንደሚያከናውኑ አቶ ክፍሌ ገልጸዋል። ምክር ቤቱ የጉራጌ ህዝብን ችግሮች ለመፍታት በተለያዩ አካላት የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ የጎላ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም