በ”አንድ ብር ለሠብዓዊነት” 120 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ያለመ መርሃግብር ተጀመረ

171

ታህሳስ 18/2014/ኢዜአ/ በመላ ኢትዮጵያ በመዘዋወር ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የሚውል 120 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብን ዓላማ ያደረገ “አንድ ብር ለሠብዓዊነት” የተሰኘ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር ዛሬ ተጀምሯል።

መርሃግብሩ ስለ ፍቅር ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ከኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን እና ከአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ጋር በመተባበር የሚያካሂደው ነው።

የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል አጥናፉ በሰጡት መግለጫ ሕዝቡን በማስተባበርና ከአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ጋር በመሆን በመዲናዋ ሁሉም ክፍለከተሞች የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ይካሄዳል ብለዋል።

በተጨማሪም በመላ አገሪቷ ከእምነት ተቋማት፣ ከትምህርት ቤቶች፣ ከመንግሥትና ከግል ተቋማት እንዲሁም ከተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር በመተባበር ለመሥራት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ በአገሪቷ ወቅታዊ ሁኔታ ለተጎዱና ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ከአንድ ብር ጀምሮ ያለውን በመለገስ ተሳትፎ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ የደንበኞች አገልግሎትና የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ኤፍሬም ጋዲሳ፤ ቲአትር ቤቱ በጎ አድራጎት ድርጅቱ በመዲናዋ ተንቀሳቅሶ ለተቸገሩ ወገኖች ገቢ ሲያሰባስብ  የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ዜጎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ ቦታዎች ማዕከል በማቋቋምና መረጃ በማሰባሰብ ድጋፉን መቀጠሉንም እንዲሁ።

የተለያዩ ሰዎች በግልና በቡድን ሆነው ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ድጋፉ በአንድ ማዕከል ካልተመራ ድግግሞሽ ያላቸው ድጋፎች እንዲኖሩና ብክነትም እንደሚያስከትል አንስተዋል።

በመሆኑም በጎ አድራጎት ድርጅቱ ከኮሚሽኑ ጋር መሥራቱ ችግሩ እንዳይፈጠር እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት።

ስለ ፍቅር ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት በተለይ በጎዳና ተዳዳሪዎችና በሴቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ መሆኑ ተነግሯል።