የዳያስፖራው ወደ አገር ቤት ጉዞ የሕይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች "የምስጋና ጉዞ" ነው

67

ታህሳስ 18/2014 ( ኢዜአ) "የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ የሕይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች ምስጋና ልናቀርብ ይገባል" ሲሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ አስገነዘቡ።

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ የተባበረ የዳያስፖራ ጥምረት 'የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ የአገር ቤት የጉዞ ጥሪ' እና የጥምረቱን ምስረታ አስመልክቶ ያዘጋጀው የበይነ መረብ ውይይት ትናንት ተካሄዷል።

ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት የሚያደርገው 'የምስጋና ጉዞ' መሆኑን አምባሳደር ታዬ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ የሕይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ ወገኖች ምስጋና ልናቀርብ ይገባል፤ ጀግኖችን ማበረታታትና ማድነቅም ያስፈልጋል ብለዋል።

"ጀግኖች ስቃይና መከራን ተሸክመው፣ የመጣባቸውን መአት ተቋቁመው፣ ሕይወታቸውን ገብረው አገር አልባ ከመባል አድነውናል" ያሉት አምባሳደሩ እነዚህ ጀግኖች ወገኖች ምስጋና እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

የዳያስፖራው የአገር ቤት ጉዞ የተስፋ ጉዞ እንደሆነ፣ ኢትዮጵያዊያንም የኢትዮጵያ ሕልውና ዘብ መሆናቸው ለዓለም የሚታይበት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ገልጸዋል።

"ጉዞው ለኢትዮጵያ መድህንና ጽናት የሚደረግ ነው፤ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ የሚደረግ ጉዞ ነው" ሲሉ ነው የገለጹት አምባሳደር ታዬ።

የዳያስፖራው ጉዞ ኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና ለሚያደርጉና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሳይታክቱ ለሚሰሩ ሃይሎች ትልቅ ፖለቲካዊ መልዕክት እንዳለውም አመልክተዋል።

የምንሄደው ተስፋና እውነት ወዳላት ኢትዮጵያና ሃቀኛ ወደ ሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤ ለዓለምም ኢትዮጵያ በችግር ጊዜ ጸንታ የምትቆምና የምትቀጥል አገር መሆኗን በተግባር እናሳያለን ብለዋል።

"ኢትዮጵያ ሲፈልጉ የሚሰሯት፣ ሲፈልጉ የሚጠግኗት፣ ያሻቸውን የሚግቷት አይደለችም፤ የእኛ ኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነቷን አስከብራ ቆይታለች አሁንም አስከብራ ትቀጥላለች" ነው ያሉት አምባሳደሩ።

ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ጉዞ በመሳተፍ በአገራችን ጉዳይ የማንደራደር መሆናችንን ማሳየት ይጠበቅብናል በማለት ጉዞው ከምንም በላይ በዋናነት ፖለቲካዊ መልዕክት እንደሆነ ተናግረዋል።

"ይህ ጉዞ የመዳን ጉዞ ነው" ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ አሁን ቁስሉ የሚሸርበትና የሚድነበት ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያዊነት ትዕግስት፣ አርቆ አሳቢነት፣ ጽናትን የተላበሰ ማንነት እንጂ፤ ኢትዮጵያዊነት የአፍታ ደስታ፣ የቅጽበት ጊዜ ትካዜ አይደለም" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጽናት የሚመነጨው ከኢትዮጵያዊያን ሠላም ወዳድነት እንደሆነና አለመግባባቶችን በመነጋገርና በውይይት ዘላቂ ሠላም ማረጋገጥ አንደሚገባ አመልክተዋል።

ከፉክክር ይልቅ ትብብር፣ ከመገፋፋት ይልቅ መተባበር ያስፈልጋል ያሉት አምባሳደር ታዬ "ከተባበርን እንድናለን፣ ከተከፋፈልን እንወድቃለን" ብለዋል።

ደጉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚታወቀው ትህትናውና እንግዳ ተቀባይነቱ ዳያስፖራውን እንደሚያስተናግድ ያላቸውንም እምነት ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ ኢትዮጵያ ኑ አገራችሁን ታደጓት" ሲሉም አምባሳደር ታዬ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም