በአፋር ክልል አሸባሪው በህወሃት ቡድን ወረራ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ወገኖች 17 ሚሊዮን ብር የሚገመት ምግብና አልባሳት ድጋፍ ተደረገ

204

ሰመራ፤ ታህሳስ 18/2014 (ኢዜአ) በውጭና ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ተቋማት አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአፋር ክልል በፈጸመው ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብና አልባሳት ድጋፍ አደረጉ ።

ድጋፍ ካደረጉት መካከል  ኢሳት ቴሌቪዥን በአሜሪካ ሎሳንጀለስ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ ቁሶችን በማሰባሰብ ለክልሉ ያስረከበው ከፍተኛው ነው።

በርክክቡ ስነ-ስርዓት ወቅት የኢሳት ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ መታሰቢያ ቀጸላ እንደገለጸችው፤ በአፋር ክልል በሽብር ቡድኑ ጥቃት የተፈናቀሉ ወገኖችን ችግር  ታሳቢ በማድረግ ነው ድጋፉ የተመቻቸው።

ከድጋፉ ውስጥ የዳቦ ዱቄት፣ሩዝ ፣የህጻናት አልሚ ምግብና ዘይት  እንደሚገኝበት ጠቅሳ፤  በቀጣይም ተጎጂዎችን በዘላቂነት እስኪማቋቋም ድረስ እንደሚቀጥል አስታውቃለች።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ በበኩላቸው፤የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች ለተጎጂ ወገኖች ድጋፍ እንዲውል ከደመወዛቸው በመቀነስ ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የተለያዩ የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ የሽብር ቡድኑ በፈጸመው ወረራ የተፈናቀሉ ወገኖችን መደገፍ የሁሉም ዜጋ ግዴታ መሆኑን የቢሮው ሃላፊ ተናግረዋል።

ከዚህም ሌላ በአንጎላ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አባላት በአሻባሪው ወረራ ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ወገናዊ አጋርነታቸውን ለመግለጽ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የተለያዩ የምግብ እህል ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለጹት ደግሞ ድጋፉን ያስረከቡት  የኮሚኒቲው ተወካይ አቶ አወል ሜኤ ናቸው።

ድጋፉን የተረከቡት የአፋር ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መሀመድ ሁሴን እንደተናገሩት፤ የሽብር ቡድኑ ዜጎችን በማፈናቀልና መሠረተ ልማቶችን በማውደም ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አድርሷል።

በዚህም በክልሉ  የተለያዩ ወረዳዎች  ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ለችግር መጋለጣቸውን አስረድተዋል።

በሀገር ውስጥም ሆነ  ውጭ  የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ችግር ላይ የወደቁ ወገኖችን ለመርዳት እያሳዩት የሚገኘው ወገናዊ አጋርነት  የሚያኮራ መሆኑን ገልጸው፤ ድጋፍ ላደረጉት አካላት  በክልሉ መንግስትና በተጎጂዎች ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በወረራው ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመርዳት  የክልሉና የፌደራል መንግስት እያደረጉ ካሉት ጥረቶች በተጨማሪ ሁሉም ዜጋ የቆየ  ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት ባህሉን በማጎልበት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።