ርዕሰ መስተዳድሩ ለብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ምስጋና አቀረቡ

293

ታህሳስ 18/2014 ( ኢዜአ) አገርና ሕዝብ በተቸገሩ ጊዜ ለደረሱ እንደ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ያሉ አገር ወዳድ ባለውለታዎችን ማክበርና ምስጋናም ማቅረብ እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ።

ዶክተር ይልቃል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስን የአገር ባለውለታነት በማሰብ በወልድያ ኪዳነ ምህረት ቤተ-ክርስቲያን በመገኘት ምስጋና አቅርበውላቸዋል።

ምስጋና የማቅረባቸው ምክንያት ብፁዕነታቸው የህወሓት የሽብር ቡድን ወልድያና አካባቢዋን በወረረ ጊዜ ለሕዝቡ እውነተኛ ጠባቂ አባት መሆናቸውን በተግባር በማስመስከራቸው ነው።

የአካባቢው ሕዝብ በጭንቅ ውስጥ በነበረበት ወቅት ዘርና ሃይማኖት ሳይለዩ ለሁሉም በእኩልነት ሲያደርጉ የነበረው ድጋፍ ለማንኛውም እምነት ተከታይ አርአያ የሚሆን ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል።

እኚህ የኃይማኖት አባት ነዋሪው ያለውን ተካፍሎ እንዲበላ ከማድረግ ባሻገር ሕሙማን መድሃኒት እንዳያጡ የተቻላቸውን በማድረግ የሕዝብ አለኝታ ሆነው መቆታቸውንም ነው ዶክተር ይልቃል የተናገሩት።

“አቡነ ኤርሚያስ የቤተ-ክርሰቲያን መሪ ብቻ ሳይሆኑ የሰውነት ውሃ-ልክ፤ በክፉ ቀንም ሕዝብን ያሻገሩ አባት ናቸው” ብለዋል።

ዶክተር ይልቃል ብፁዕነታቸው ሰውን በሰውነቱ ብቻ ያለ ልዩነት ያገለገሉ፣ ሕዝቡን ጽናት በማስተማርና ሥርዓትን አስጠብቆ በማቆየት ለእምነት አባቶችና ለኢትዮጵያዊያን አርዓያ የሚሆን ተግባር የፈፀሙ ብለዋቸዋል።

ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ወራሪውን ሃይል ሲፋለሙ የወደቁ የሠራዊት አባላትን በማንሳት ሕክምናና ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ነው ዶክተር ይልቃል የገለጹት፡፡

በዋናነትም የሠራዊት አባላትን ተንከባክበው ለሌላ ምዕራፍ በማብቃት ለአገራቸው ታላቅ ውለታ መዋላቸውን አውስተዋል።

በመሆኑም እንደ እርሳቸው ያሉ ብርቅዬ አባቶችን ማክበር፣ ማድነቅና ማመስገን ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

ብጹዕነታቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሲያገለግሏቸው እንደነበረ በእርሳቸው እንክብካቤ ሲደረግላቸው የቆዩ የሠራዊት አባላት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ሃይማኖት እና ዘር ሳይለዩ ሁሉንም በእኩል በማገልገል ለአዲስ ምዕራፍ እንድንበቃ አድርገውናል ሲሉ ነው የተናገሩት የሠራዊቱ አባላት።

ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ የወልድያ እና አካባቢውን ሕዝብ በመደገፍ ለነጻነት በማብቃታቸው በተለያዩ እምነት ተከታይ ሕዝቦች ዘንድ አክብሮትና አድናቆት እየተቸራቸው ነው።