“ነጻነት እና ክብራችንን በመስዋዕትነታችን አግኝተናል፤ የወደመውንም ንብረት እንገነባዋለን”

236

ታህሳስ 18/2014 ( ኢዜአ) “ነጻነታችንን እና ክብራችንን በመስዋዕትነታችን አግኝተናል፤ የወደመውንም ንብረት ከመላ ኢትዮጵያዊያን ጋር ሆነን እንገነባዋለን” ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ፡፡

ዶክተር ይልቃል በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ የተፈጸመበትን የወልድያ ዩኒቨርሲቲን ጎብኝተዋል።

ወራሪው የህወሓት ቡድን በፈጸማቸው አስጸያፊ ተግባራት ለአማራ ብቻ ሳይሆን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን ጥላቻ አስመስክሯል ብለዋል፡፡

ትውልዱ እንዳይማር፣ በእውቀት እንዳይበለጽግና ድንቁርና እንዲስፋፋ በማለም የትምህርት ተቋማትን ማውደሙን ነው የተናገሩት፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች የመጡ ተማሪዎች የሚማሩበት ነው ያሉት ዶክተር ይልቃል፤ ለሰው ልጅ ቅንጣት ክብር የሌለው አሸባሪው ቡድን ያወደመው ይህን የእውቀት ማዕድ ነው ሲሉ ነው የገለጹት።

ቡድኑ አስነዋሪ እና ወንጀለኛ ለመሆኑ በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ላይ የፈጸመው ተግባር ብቻውን ማረጋገጫ ይሆናል ብለዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን ያወደመውን ይህን ሃብት መልሶ ለመገንባትና ለመተካት መላው ኢትዮጵያዊያን በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡

“ነጻነታችንን እና ክብራችንን በመስዋዕትነታችን አግኝተናል” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የወደመው ሃብት ቢያስቆጨንም ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሆነን መልሰን እንተካዋለን ብለዋል፡፡

ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን ወረራ ነጻ የወጡ አካባቢዎች ማኅበረሰቦችም ባለፈው መቆዘም ሳይሆን ለመጪው አዲስ ምዕራፍ መነሳሳት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

መንግስትም የወደመውን ንብረት ከሕዝቡ ጋር በመሆን መልሶ ለመገንባት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዲያቆን ተስፋሁን ባንተው በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰቡ በመሆኑ መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን የሰሜን ወሎን ዞን በወረራ በያዘባቸው ጊዜያት በርካታ ዜጎችን ጨፍጭፏል፣ ንብረት ዘርፏል፣ መዝረፍ ያልቻለውንም አውድሟል፡፡