በጦርነትና በግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መልሶ ማቋቋሚያ የ5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ተዘጋጅቷል

62

ታህሳስ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ)በጦርነትና በግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል የ 5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መዘጋጀቱን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ገለጹ፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር የሚመራው የመልሶ ማቋቋም ሴክሬታሪያት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ታህሳስ 15 2014 ዓ.ም በገንዘብ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ የመጀመሪያውን ውይይት አድርጓል።

በዚሁ ወቅት አቶ አህመድ እንደገለጹት በገንዘብ ሚኒስቴር የተዘጋጀው የ 5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን ጠቁመው ተጨማሪውን በጀት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዳጸደቀው በቀጥታ ወደ ስራ ይገባል።

መንግስት ከሚመድበው መነሻ በጀት በተጨማሪም ከልማት አጋሮች በተለይም ከአለም ባንክ ለመልሶ ማቋቋሙ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ የመልሶ ማቋቋሙ መርሀ ግብሩ በመንግስት የሚመራ፣የተቀናጀ፣ በየደረጃው በፕሮግራም ተግባራዊ የሚደረግ፣ተጠያቂነት ያለውና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚተጋ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በጦርነቱና በግጭቱ የደረሰውን ጉዳት ለማወቅና በገንዘብ ለመተመን የሚያስችል የዳሰሳ ጥ ናት ለማድረግ የሚያስችል የመነሻ ሀሳብ በገንዘብ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ለመልሶ ማቋቋም ሴክሬታያት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የቀረበ መሆኑን ተገልጿል።

የኮሚቴ አባላትም የመልሶ ማቋቋም መርሀግብሩ ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍሎች በተጨማሪ በሌሎች ክልሎች በግጭት የተፈናቀሉትንም እንዲያካትት፣የሀብት አሰባሰብ ድግግሞሽ እንዲወገድና በአንድ ቋት እንዲሰባሰብ፣ ክልሎች ንቁ ተሳትፎ የሚደርጉቡት ምቹ ሁኔታ እንዲመቻች፣ ከሌሎች መሰል ብሄራዊ ኮሚቴዎች ጋር በቅንጅት እንዲሰራና የግሉን ዘርፍና ዲያስፖራውን እንዲያሳትፉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በውይይቱ የመልሶ ማቋቋም ሴክሬታሪያቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የሆኑት የትምህርት፣ የጤና፣ የፕላንና ልማት፣ የውሃና ኢነርጂ፣ የኢንዱስትሪ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ፣ የስራና ክህሎት፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሮችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል መስሪያ ቤት አመራሮች መገኘታቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም