አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት ያስወጣችብትን ውሳኔ ልታጤነው እንደሚገባ ኢትዮጵያ አመለከተች

130

ታህሳስ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት ያስወጣችብትን ውሳኔ አጥብቃ ልታጤነው እንደሚገባ ኢትዮጵያ አመልክታለች።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ የንግድ ስርኣት ያስወጣችብትን ውሳኔ በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።

የአፍሪካ ሀገራትን በንግድና ስራ እድል ተጠቃሚ ከሚያደርገው የአጎዋ ንግድ ስርኣት አሜሪካ ኢትዮጵያን ማስወጣቷ የኢትዮጵያን መንግስት እንዳሳዘነው ነው መግለጫው ያመለከተው።

የኢትዮጵያ መንግስት ሰላምና መረጋጋትን ፣ፖለቲካዊ መግባታትና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ሊያመጡ የሚችሉ ስራዎችን ባለፉት ሦስት ዓመታት ማከናወኑን ያመለከተው መግለጫው በተለይ ደግሞ የሁለቱን አገራት ረጅም ጊዜ የቆየ ግንኙነት ያማከለ የለውጥ ስራዎች መከወኑንም አንስቷል።

ከአሜሪካ ልዩ ልዩ ተቋማት ጋር ደግሞ የሁለትዮሽ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ግንኙነቱን ለማጠንከር እየተሰራ መሆኑን ያብራራው መግለጫው ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ማስወጣት በአጎዋ የስራ እድል የተፈጠረላቸውን በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን የሚጎዳ ተግባር ከመሆን ባለፈ በእነሱ ስር ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎችንም ኑሮ የሚያመሳቅል መሆኑን አስታውቋል።

በዚህም አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት ያስወጣችበትን ውሳኔ አጥብቃ ልታጤነው እንደሚገባ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም