በኮንትሮባንድ የገቡ ከ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

164

አዳማ ፤ታህሳስ 18/2014(ኢዜአ) ከውጭ በኮንትሮባንድ ገብተው በአዳማ ከተማ ውስጥ የተገኙ ግምታቸው ከ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ዕቃዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

በከተማዋ ፖሊስ መምሪያ የደምበላ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የወንጀል መከላከል ዘርፍ ሃላፊ ኢንስፔክተር አህመድ ከድር ለኢዜአ እንደገለጹት፤  የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ  በቁጥጥር ስር የዋሉት በአንድ የንግድ ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ ነው።

የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3- 60997 ኦሮ የሆነው የጭነት ተሽከርካሪ የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹን  ጭኖ ወደ ተቋሙ ቅጥር ግቢ አስገብቶ ለመደበቅ ሲሞክር በተደረገው ክትትል መቆጣጠር እንደተቻለ ነው ያመለከቱት።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ  ልባሽ ጨርቃ ጨርቅ ፣ መድኃኒት ፣ የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችና የተሽከርካሪ  ጎማ እንደሚገኙበት ኢንስፔክተር አህመድ አስታውቀዋል።

ፖሊስ የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹን  ደብቀዋል ብሎ የጠረጠራቸውን አሽከርካሪውንና ሌላ ግለሰብ ለጊዜው ከአካባቢው ሸሽተው ቢያመልጡም በመያዝ ለህግ ለማቅረብ ክትትል እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ዕቃዎቹን በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ለአዳማ ቅርንጫፍ ማስረከባቸውን አስታውቀዋል።