የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ የሕይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች ምስጋና ልናቀርብ ይገባል

59

ታህሳስ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) “የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ የሕይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግና ወገኖች ምስጋና ልናቀርብ ይገባል” ሲሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ አስገነዘቡ።

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ የተባበረ የዳያስፖራ ጥምረት ‘የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ የአገር ቤት የጉዞ ጥሪ’ እና የጥምረቱ ምስረታ አስመልክቶ ያዘጋጀው የበይነ መረብ ውይይት ትናንት ተካሄዷል።

ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት የሚያደርገው ጉዞ የምስጋና ጉዞ መሆኑን አምባሳደር ታዬ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ የሕይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ ወገኖች ምስጋና ልናቀርብ ይገባል፤ ጀግኖችን ማበረታትና ማድነቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

“ጀግኖች ስቃይና መከራን ተሸክመው የመጣባቸውን መአት ተቋቁመው ሕይወታቸውን ገብረው አገር አልባ ከመባል አድንውናል” ያሉት አምባሳደሩ፤ እነዚህ ጀግና ወገኖች ምስጋና እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

የዳያስፖራው የአገር ቤት ጉዞ የተስፋ ጉዞ እንደሆነና ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ የሕልውና ዘብ መሆናቸውን ለዓለም የሚታይበት መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸዋል።

“ጉዞው ለኢትዮጵያ መድህንና ጽናት የሚደረግ ነው፤ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ የሚደረግ ጉዞ ነው” ብለዋል አምባሳደር ታዬ።

የዳያስፖራው ጉዞ ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያልተገባ ጫና ለሚያደርጉናና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሳይታክቱ ለሚሰሩ ሃይሎች ትልቅ ፖለቲካዊ መልዕክት እንዳለው አመልክተዋል።

የምንሄደው ተስፋና እውነት ወዳላት ኢትዮጵያና ሐቀኛ ወደ ሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤ ለዓለምም ኢትዮጵያ በችግር ጊዜ ጸንታ የምትቆምና የምትቀጥል አገር መሆኗም በተግባር እናሳያለን ብለዋል።

“ኢትዮጵያ ሲፈልጉ የሚሰሯት ሲፈልጉ የሚጠግኗት የሚፈልጉትን የሚግቷት አይደለችም፤ የእኛ ኢትዮጵያ ክብራችንንና ሉዓላዊነታቸውን አስከብራ ቆይታለች አሁንም አስከብራ ትቀጥላለች” ነው ያሉት አምባሳደር ታዬ።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዚህ ጉዞ በመሳተፍ በኢትዮጵያ ጉዳይ የማንደራደር መሆናችንን ማሳየት ይጠበቅብናል በማለት፤ ጉዞው ከምንም በላይ በዋናነት ፖለቲካዊ መልዕክት እንደሆነም አመልክተዋል።

ይህ ጉዞ የመዳን ጉዞ ነው ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ አሁን ቁስሉ የሚሸርበትና የሚድነበት ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያዊነት ትዕግስት አርቆ አሳቢነት ጽናትን የተላበሰ ማንነት ነው፤ የኢትዮጵያዊነት የአፍታ ደስታ የቅጽበት ጊዜ ትካዜ አይደለም” ብለዋል አምባሳደሩ።

የኢትዮጵያ ጽናት የሚመነጨው ከኢትዮጵያውያን ሰላም ወዳድነት እንደሆነና አለመግባባቶችን በመነጋገርና በመወያየት ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ አንደሚገባ አመልክተዋል።

ከፉክክር ይልቅ ትብብር ከመገፋፋት ይልቅ መተባበር ያስፈልጋል ያሉት አምባሳደር ታዬ ከተባበርን እንድናለን ከተከፋፈልን እንወድቃለን ብለዋል።

ደጉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚታወቀው ትህትናውና እንግዳ አቀባበሉ ዳያስፖራውን እንደሚያስተናግድ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ኢትዮጵያ ኑ አገራችሁን ታደጓት” ሲሉ አምባሳደር ታዬ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም