ገንዘብ ዘርፎ ቱቦ ውስጥ የገባውን ሌባ ታግለው እጅ ከፍንጅ በመያዝ ገድል የሰሩት ዋና ሳጅን አናቶ

102

ታህሳስ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከአውቶብስ ውስጥ ገንዘብ ዘርፎ ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ ውስጥ የገባውን ሌባ ታግለው እጅ ከፍንጅ በመያዝ ገድል የሰሩት የፖሊስ አባል ዋና ሳጅን አናቶ አርጎ።

ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ ታህሳስ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ቀትር ላይ ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ትኬት የቆረጠ ተሳፋሪን ለመጫን ሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ፊት ለፊት ይቆማል።

አውቶቡሱ በቆመበት ቅጽበት ሁለት ሰዎች ተሳፋሪ መስለው በመግባት ከአውቶቡሱ ውስጥ ፊት ለፊት ባለው  "ዳሽ ቦርድ" ላይ የተቀመጠን 12 ሺህ ብር ሰርቀው መሮጥ ይጀምራሉ።

ድርጊቱን የተመለከቱት የአውቶቡሱ ረዳትና ገንዘብ ያዥ ሌቦቹን ለመያዝ እየተጫጯሁ ሲከተሏቸው አንደኛው በአካባቢው በነበሩ የሲዳማ ክልል ፖሊስ ልዩ ኃይል በቁጥጥር ስር ሲውል ገንዘቡን የያዘው ደግሞ መንገድ ዳር ባለ ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ  ውስጥ ይገባል።

ስለሁኔታው መረጃ የደረሳቸው በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የአዲስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የወንጀል መከላከል ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ ዋና ሳጅን አናቶ አርጎ ፈጥነው በስፍራው ይደርሳሉ።

እንደደረሱም ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ  ውስጥ የገባው ሌባ ውጣ ቢባልም ላለመውጣት ድንጋይ እየወረወረ ለመከላከል ይሞክራል።

ፖሊስ ገንዘብ ቀምቶ የተደበቀውን በቁጥጥር ስር በማዋል ሚናውን መወጣት እንዳለበት የሚናገሩት ዋና ሳጅን አናቶ፤  በልበ ሙሉነት ሌባው የገባበት ቱቦ ውስጥ ሳያመነቱ ገቡ።

ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ ውስጥ ወደ 150 ሜትር ከተጓዙ በኋላ ግን ውስጡ ጠባብና ከፍተኛ ሙቀት  ስለነበር ወበቅና ለመተንፈስም ጭንቅ ሆኖባቸው  እጅጉን ተቸግረው እንደነበር ሳጅን አናቶ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ችግሩን ተቋቁመው ውስጥ ለውስጥ እስከ 300 ሜትር በመጓዝ ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ ውስጥ የተደበቀው ቀማኛ እጁን እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ቢጠይቁትም ፈቃደኛ ሳይሆን እንደታገላቸው ነው ያመለከቱት።

በሃይላንድ ፕላስቲክ ክምር ውስጥ በመደበቅ እራሱን ለመሰወር ጥረት ቢያደርግም ከአንድ ሰዓት ተኩል ብርቱ ጥረት በኋላ  ሌባውን ከቱቦው ውስጥ ይዘው በማውጣት መቆጣጠር እንደቻሉ  ዋና ሳጅን አናቶ አስረድተዋል።

ግለሰቡ አውቶቡስ ውስጥ የሰረቁት ገንዘብ በሙሉ ይዞ ውስጥ እንደገባ በወቅቱ በስፍራው ከነበሩ የዓይን እማኞች  መረዳት ቢቻልም  ከ2 ሺህ 100 ብር ጋር ብቻ እጅ ከፍንጅ ተይዞ ቀሪውን ለማግኘት ተጨማሪ ምርመራና የማጣራት ስራ እየተካሄደ  መሆኑን ዋና ሳጅኑ  አስታውቀዋል።

ህብረተሰቡ ይህንን መሰል የዘረፋና ንጥቂያ ወንጀል  ተግባር የሚፈፅሙ ግለሰቦችን በመያዝም ሆነ በማጋለጥ ከሚመለከተው የሕግ አካል ጋር በትብበር እየሰራ መሆኑንም አውስተዋል።

ዘረፋ የተፈጸመበት የአውቶቡሱ ገንዘብ ያዥ አቶ አዲሱ ሙሉ በስልክ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ትኬት የቆረጡ ሰዎችን ለማሳፈር በቆሙበት ቅጽበት ግለሰቦቹ የዘረፋ ወንጀል እንደፈጸሙባቸው ተናግረዋል።

ተሳፋሪውን እስኪጭኑ ድረስ ሁለቱ ሌቦች ተሳፋሪና ሹፌሩ እያያቸው ገንዘብ ካስቀመጡበት "ዳሽ ቦርድ" ላይ ከመቀጽበት አንስተው እንደሮጡ አስረድተዋል።

ተከታትለው ለመያዝ ጥረት ቢያደርጉም ገንዘቡን የያዘው ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ ውስጥ በመግባቱ እንዳልተሳካለቸው ገልጸው፤ በመጨረሻ በፖሊስ ጥረት በመያዙ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ሁለቱም ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ በመሆኑ የተዘረፈው ገንዘብ ይገኛል ብለው እንደሚጠብቁ ነው የገለጹት።

የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ተስፋዬ ቱንጋሞ በበኩላቸው፤  የከተማዋ ፖሊስ አባል ራሱን ለአደጋ በማጋለጥ  የፈፀመው ገድል ለሌሎች የፀጥታ አካላት አርአያ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ዓይነት ንጥቂያና ዘረፋ በከተማዋ በሁሉም ኮርደሮች እንደሚስተዋል ጠቅሰው፤ ድርጊቱን በተጠናና በተደራጀ አግባብ ለመከላከል በተከናወነው ስራ እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል።

በተለይ  የመጪዎቹን በዓላት ምክንያት በማድረግ ዲያስፖራዎች ወደ ክልሉ እየገቡ በመሆኑ  ካለምንም ስጋት እንዲቀሳቀሱ በየደረጃው የፀጥታ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ጠንካራ የወንጀል የመከላከል ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ክልሉ ፍፁም ሰላማዊ እንደሆነ ያመለከቱት ኮሚሽነሩ፤ በዓላቱ  በሰላም እንዲከበሩ ፖሊስ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁንም አስታውቀዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም