ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በሊቀጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ

77

ታህሳስ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በሊቀጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት የሀዘን መግለጫ መልዕክት የነጻነት ትግል ተምሳሌት እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

በሊቀጳጳስ ቱቱ ህልፈት ኢትዮጵያ የተሰማትን ሀዘን ለደቡብ አፍሪካ ህዝብና መንግስት ትገልጻለች ብለዋል።

እ.አ.አ በ1931 የተወለዱት ሊቀጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ በ23 ዓመታቸው ከደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የመምህርነት ስራ ቢጀምሩም ከሶስት ዓመት በኋላ የስነ-መለኮት ትምህርት በመከታተል እ.አ.አ በ1960 ቅስና ተቀብለዋል።

ከዚያም ከሁለት ዓመት በኋላ ወደ እንግሊዝ በማቅናት ለአራት ዓመታት የስነ-መለኮት ትምህርታቸውን ቀጥለው የማስተርስ ዲግሪ ተቀብለዋል።

ወደ አገራቸው ተመልሰውም ስነ መለኮት ሲያስተምሩ ቆይተዋል።በድጋሚ ወደ እንግሊዝ በማቅናትም በለንደን በሚገኝ የስነመለኮት ኢንስቲትዩት ረዳት ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል።

ወደ ደቡብ አፍሪካ ተመልሰውም የሴይንት ሜሪ ካቴድራል የመጀመሪያው ጥቁር ዲን ሆነው ሰርተዋል።

እ.አ.አ በ1978 ደግሞ የደቡብ አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት የመጀመሪያው ጥቁር ዋና ጸሐፊ በመሆን መርተዋል።

ከብሪታኒያ፣ ጀርመንና አሜሪካ ለነበራቸው አገልግሎት የተለያየ የክብር ዶክትሬት ተቀብለዋል።

የዘር መድሎን በጽኑ ይታገሉ የነበሩት ሊቀጳጳስ ቱቱ እኩል የሲቪል መብት ለሁሉም፣ የደቡብ አፍሪካ የፓስፖርት ህግ እንዲታገድና ወጥነት ያለው ስርዓተ ትምህርት እንዲኖር ከፍተኛ ትግል በማድረግ ይታወቃሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም