በሆስፒታሉ በነፃ የሚሰጠው 'የንግግር ሕክምና' በባለሙያ እጥረት ታካሚዎችን ረጅም ጊዜ እያስጠበቀ ነው

129

ታህሳስ17/2014/ኢዜአ/ በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ብቻ የሚሰጠው ነፃ የንግግር ሕክምና ወይንም ስፒች ቴራፒ በባለሙያ እጥረት ምክንያት ታካሚዎችን ለረጅም ወረፋ መጠበቅ እየዳረገ ነው ሲሉ ባለሙያዎችና አስታማሚዎች ገለጹ።

የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ የሕክምና አገልግሎቱን ለማስፋትና የባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብሏል።

የንግግር ሕክምና /ስፒች ቴራፒ/ ከከንፈርና ላንቃ ቀዶ ሕክምና በኋላ፣ በአዋቂዎች ከአደጋና በጭንቅላት ውስጥ ከሚከሰት የደም መፍሰስ /ስትሮክ/ ጋር ተያይዞ ለሚከሰት የንግግርና የማስታወስ ችግር፣ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸውና የንግግር መዘግየት ላጋጠማቸው ልጆች የሚሰጥ ሕክምና ነው።

ይህ ሕክምና በአዲስ አበባ የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በነጻ እየተሰጠ ይገኛል።

ይሁንና በሆስፒታሉ ለሕክምና የመጡ ተገልጋይና የኮሌጁ የስነ-ልሳን ባለሙያ እንደሚሉት ሕክምናውን የሚሰጡት ባለሙያዎች ሁለት ብቻ መሆናቸው ታካሚዎች ለዓመታት ወረፋ እንዲጠብቁ አድርጓል ይላሉ።

በሆስፒታሉ ልጃቸውን የሚያሳክሙት አቶ ዳኛቸው አሰፋ ለኢዜአ እንደገለፁት በኮሌጁ ሕክምና የሚሰጡ ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ታዝበዋል።

ይህ በመሆኑ ደግሞ ታካሚዎች ውጤታማ የሆነ አገልግሎት እንዳያገኙ አድርጓል ነው ያሉት።

ሕክምናው በነጻ በመሰጠቱ ደስተኛ መሆናቸውን የሚገልጹት አቶ ዳኛቸው የባለሙያዎችን ቁጥር ጨምሮ ታካሚዎች የተሻለ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ቢደረግ መልካም ይሆናል ብለዋል።

በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የስነ-ልሳን ባለሙያ አካሉ አሰፋ በበኩላቸው በተለያየ ምክንያት የማስታወስና የንግግር መዘግየት ለገጠማቸው ሰዎች 'የንግግር ሕክምና' እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ኮሌጁ አገልግሎቱን መስጠት ከጀመረ ሁለት ዓመት መቆጠሩን ገልፀው በቀን እስከ 19 ሰዎች የንግግር ሕክምናና የማማከር አገልግሎት እንደሚያገኙም ተናግረዋል።

ሆኖም አገልግሎቱን የሚሰጡ ባለሙያዎች ቁጥር ሁለት ብቻ በመሆኑ ታካሚዎች ለረጅም ጊዜ ወረፋ እንዲጠብቁ ማድረጉንና ባለሙያዎቹም ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሕክምናውን በስፋት ለመስጠትና ውጤታማ ለማድረግ የባለሙያዎችን ቁጥር ማሳደግ ግድ እንደሚልም ነው የገለጹት።

እንደ አገር የስነ-ልሳን ባለሙያዎች እጥረት መኖሩን የገለፁት የጤና ሚኒስቴር የሰው ሀብት ልማት ዳይሬክተር አቶ አሰግድ ሳሙኤልም አገልግሎቱን ለማስፋትና የባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር እየተሰራ ነው ይላሉ።

የአጭር ጊዜ ስልጠናውን ለመስጠት የጤና ተቋማት የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል።

መደበኛውን የሆስፒታል አገልግሎት በማይጎዳ መልኩ ስልጠናውን ጎን ለጎን ለማስኬድ ታስቧልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም