ክልሉ ለማዕከላዊ ገበያ ያቀረበው ቡና ደረጃ አንድ አስመዝግቧል

112

ዲላ ፤ ታህሳስ 17/2014(ኢዜአ)የደቡብ ክልል ዘንድሮ ለማዕከላዊ ገበያ ያቀረበው ከ5 ሺህ 800 ቶን በላይ ቡና ደረጃ አንድ በማስመዝገብ ካለፉት ዓመታት መሻሻል ማሳየቱን የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን አስታወቀ።

የክልሉ ቡና አምራች ሞዴል አርሶ አደሮች በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማ የቡና ማሳን በመስክ ተመልክተዋል።

ክልሉ  በተያዘው በጀት ዓመት ከ46 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለመላክም እየሰራ መሆኑን ነው የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሬድዋን ከድር በወቅቱ የገለጹት።

በክልሉ በዘመኑ  የቡና ጥራትን በማሻሻል፣ በምርት አሰባሰብና በግብይት ላይ በተደረገው ቁጥጥር ውጤት መገኘቱን አስረድተዋል።

በዚህም  ክልሉ ለማዕከላዊ ገበያ ያቀረበው ከ5 ሺህ 800 ቶን በላይ  ቡና በጥራቱ ቀዳሚ የሚያደርገውን ደረጃ ማግኘቱን አስታውቀዋል።

የክልሉ ቡና ከዚህ ቀደም በአብዘኛው የሚያገኘው ደረጃ ሁለትና ከዚያ በታች ባሉት ደረጃዎች እንደነበር አስታውሰው፤የዘንድሮው አቅርቦት በጥራት ያመጣው ለውጥ አበረታች እንደሆነ ገልጸዋል።

ክልሉ ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበው ልዩ ጣዕም ያለው  ቡናም የጥራት ደረጃው ለማሻሻል አስተዋጽኦ ማድረጉን አቶ ሬድዋን አብራርተዋል።

የክልሉ ቡና ጥራትን በዘላቂነት በማስጠበቅ የአርሶ አደሩን ብሎም የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም ለቡና እድሳት ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል።

አርሶ አደሩ ከልማዳዊ አሰራር ተላቆ የተሻሻሉ አሰራሮችን በመጠቀም ቡናን በኩታ ገጠም እንዲያለማ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተው፤ ለዚህም የጌዴኦ ዞንን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ቡናን በኩታ ገጠም ማልማት ከምርታማነትና ከጥራት ባለፈ ለእርሻ መሬት አጠቃቀም ወሳኝ በመሆኑ የክልሉ ሞዴል ቡና አምራች አርሶ አደሮች በመስክ ምልከታው ያገኙትን በሥራ ላይ እንዲያውሉትም አሳስበዋል።

''ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የግብርና አሰራርን በማዘመን ቴክኖሎጂ መጠቀም ግዴታ ነው'' ያሉት ደግሞ በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ ልምዳቸውን ያካፈሉት ሞዴል አርሶ አደር ደሳለኝ ዶጎማ ናቸው።

በአራት ሄክታር ማሳቸው ላይ ለሁለት ዓመታት ያከናወኑት የቡና እድሳት ተጠቃሚ አድርጎኛል ብለዋል።

በተለይ ከምርምር ተቋማት ያገኟቸውን የቡና ችግኞች ዘመናዊ አሰራርን ተጠቅመው በመትከላቸውና እንክብካቤ በማድረጋቸው በሄክታር ከ12 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘታቸውን አርሶ አደር ደሳለኝ ገልጸዋል።

በመስክ ምልከታው የተሳተፉት ከሀዲያ ዞን የጊቤ ወረዳ ሞዴል አርሶ አደር ሃይለማርያም ኤርባሎ፤  ከአምስት ሄክታር የቡና ማሳቸው በዓመት የሚያገኙት ምርት ከስድስት ኩንታል እንደማይበልጥ ተናግረዋል።

ይህም የጌዴኦ ዞን የተሻሻሉ አሰራሮች ተጠቃሚ አርሶ አደሮች በግማሽ ሄክታር የሚያመርቱት መሆኑን አመላክተዋል።

በቀጣይ ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ምርት የማይሰጠውንና ያረጀ ቡናቸውን በመተካትና በመጎንደል ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እንደሚጥሩ ገልጸዋል።

በመስክ ምልከታው  የክልሉ ቡና አምራች ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ሞዴል አርሶ አደሮች፣ የዘርፉ አመራሮችና  ባለሙያዎች መሳተፋቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም