አሸባሪው ህወሓት ከ300 ሺህ በላይ ሕዝብ ይጠቀምበት የነበረውን የመርሳ ሆስፒታልን አውድሞታል

198

ታህሳስ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት የመርሳን ሆስፒታል ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የሕክምና ቁሳቁስ በመዝረፍ እንዲሁም መውሰድ ያልቻለውን ሙሉ በሙሉ ማውደሙን የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ገለጹ፡፡

የመርሳ ሆስፒታል ከ300 ሺህ በላይ ሕዝብ የሚገለገልበት እንደነበረ ተገልጿል።

የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ አድማሱ ተስፋዬ የሕዝብ ጠላት መሆኑን በአስነዋሪ ተግባራቱ ያስመሰከረው አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ወሎ ሀብሩ ወረዳ መርሳ ከተማ የሚገኘውን መርሳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሙሉ በሙሉ አውድሞታል ብለዋል።

ሆስፒታሉ ለሀብሩ ወረዳ፣ ለመርሳ ከተማ፣ ለአጎራባች ወረዳዎችና ለአጎራባቹ የአፋር ክልል ሕዝብ ጭምር አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል።

ሀብሩ ሆስፒታል ሙሉ የሕክምና መሣሪያ የተሟላለትና የተሻለ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበረም ተናግረዋል።

ይሁንና አሸባሪው ህወሓት መርሳ ከተማን በወረረበት ጊዜ በከፍተኛ ወጪ የተገዙ የሕክምና መሳሪያዎችን በመዝረፍና የተቀሩትንም በማውድም ሆስፒታሉን ባዶ አስቀርቶታል ነው ያሉት።

የተለያዩ የምርመራ ማሽኖችን የዘረፈው የሽብር ቡድኑ የሕሙማን መገልገያ መሳሪያዎችን ጨምሮ የተመላላሽ ታካሚ ክፍሎች ላይም ውድመት ማድረሱን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በሆስፒታሉ ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የሕክምና መሣሪያዎችን ዘርፏል፣ መዝረፍ ያልቻለውንም ሙሉ በሙሉ አውድሟል ብለዋል አቶ አድማሱ።

ሆስፒታሉን ዳግም ስራ ለማስጀመር ጤና ሚኒስቴር ባመቻቸው መሰረት የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በአጭር ጊዜ የሆስፒታሉን ቁሳቁስ አሟልቶ ወደ ስራ ለማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

አቶ አድማሱ ሆስፒታሉን ዳግም ስራ ለማስጀመር በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ የአካባቢው ተወላጆች የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።