ሆቴሎች ከመስተንግዶ ጎን ለጎን ለዳያስፖራው በመዲናዋ የጉብኝት ፓኬጅ አዘጋጅተዋል

74

ታህሳስ 17/2014/ኢዜአ/ ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ የዳያስፖራ አባላት ከሚያደርጉት መስተንግዶ ጎን ለጎን ጉብኝት የሚያደርጉበትን ፓኬጅ ማዘጋጀታቸውን በአዲስ አበባ የሚገኙ ሆቴሎች ገለጹ።

መጪዎቹን የገና እና ጥምቀት በዓላት በአገር ቤት ለማክበር የሚመጡ ቱሪስቶችን ለማስተናገድ የሚደረገው ዝግጅት ተገባዷል።

ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአገር ቤት ቆይታቸው የማይረሳ ጊዜ እንዲያሳልፉ ጥሩ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑንም ኢዜአ ያነጋገራቸው በመዲናዋ የሚገኙ ሆቴሎች ገልጸዋል።

አብዛኞቹ የዳያስፖራ አባላት ከቤተሰብና ከአገርኛ ትዝታዎች ርቀው የቆዩ በመሆናቸው በምንሰጣቸው አገልግሎቶች ትዝታዎቻቸውን የሚመልሱ መርሃ ግብሮች ቀርጸናል ይላሉ ሆቴሎቹ።

ባህላዊ እሴቱን የጠበቀ የቡና ሥነ-ስርዓት፣ ባህላዊ ምግቦችና ዝግጅቶች ከመርሃ ግብሮቹ መካከል ይገኙበታል።  

የጎልደን ቱሊፕ ኢንተርናሽናል ሆቴል ማኔጀር አቶ ደረጀ ቦጋለ ዳያስፖራውን ለማስተናገድ ቀደም ሲል ከነበረን የአገልግሎት ዋጋ እስከ 35 በመቶ ቅናሽ አድርገናል ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ደረጀ ገለጻ በሆቴሉ የሚስተናገዱ ተጠቃሚዎች ለኮሮና ቫይረስ እንዳይጋለጡ የተለያዩ የመከላከያ መንገዶች ይተገበራሉ።

የቦሌ አምባሳደር ሆቴል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ሙሉጌታም ዋናው ዝግጅታችን ዳያስፖራው በቆይታው ተደስቶ እንዲሄድ እንጂ ለምናገኘው ገንዘብ አይደለም ብለዋል።  

ለዚህም ዳያስፖራው ደህንነቱ ተጠብቆ አገልግሎት እንዲያገኝ የጸጥታ አካላትን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብረን እየሰራን ነው ሲሉ ነው የገለጹት።

ዳያስፖራው በግንባርም በውጭም የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑን አስመስክሯል ያሉት የቤስት ዌስተርን ፕላስ ፐርል አዲስ ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሴፍ ሃይለየሱስ "የኢትዮጵያ ኩራት የሆኑ ዜጎቻችንን ማስተናገድ ለእኛ ኩራት ነው" ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎችን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅተናል ሲሉ ነው የተናገሩት።

የግራንድ ፓላስ ሆቴል ሴልስ እና ማርኬቲንግ ማኔጀር አዜብ አበበ በበኩላቸው የአዲስ አበባ የቱሪስት መዳረሻነት መስፋት ለእኛ መልካም አጋጣሚ ነው ይላሉ።  

ዕድሉን ለመጠቀም በሆቴላቸው የሚገለገሉ ዳያስፖራዎች ወዳጅነት አደባባይ፣ አንድነት እና እንጦጦ ፓርኮችን የሚጎበኙበትን ሥርዓት መዘርጋታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም